የሀገር ውስጥ ዜና

ለቀዳማዊ ልጅነት የተሰጠው ልዩ ትኩረት የትውልድ ግንባታንና ብልጽግናን እውን የማድረግ ራዕይን የሚያጸና ነው

By Yonas Getnet

November 22, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 13፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመደመር እሳቤ ለቀዳማዊ ልጅነት የተሰጠው ልዩ ትኩረት የትውልድ ግንባታን እና ብልጽግናን እውን የማድረግ ራዕይን የሚያጸና ነው አሉ የአፍሪካ የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ማዕከል ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር መሠረት ዘላለም።

ምክትል ሥራ አስፈጻሚዋ እንደገለጹት፤ በመንግሥት ደረጃ ትውልድን ማዕከል ያደረጉና ነገን የተሻለ የሚያደርጉ ሥራዎችን ለመሥራት ግልጽ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸው ይህም በመደመር እሳቤ ውስጥ የትውልድ ግንባታን እና የነገን ብልጽግና መሠረት የማስያዝ ራዕይን የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል።

የቀዳማዊ ልጅነት ልማት ለአንድ ሀገር ነገ ተስፋ ሰጪ ትውልድን ለማፍራት፣ የዜጎችን ስብዕና ለመገንባት እንዲሁም የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ መሠረት መሆኑን ጠቁመው፤ ዘርፉ ከመቼውም ጊዜ በላይ በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት ያገኘበት ወቅት ነው ብለዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት ሥራ፣ የሥርዓተ ምግብና የሌማት ትሩፋት ተግባራት፣ እንዲሁም የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት ለመቀነስና ጤናቸውን ለማሻሻል የተከናወኑ ሥራዎች የትውልድ ግንባታ ጥረቶች አካል መሆናቸውን አብራርተዋል።

ማዕከሉ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማም በአዲስ አበባ የተገኙ ተሞክሮዎችን በከተማዋ ብቻ ሳይገድቡ ለሌሎች ክልሎች፣ ከተሞች እንዲሁም ለአፍሪካ ሀገራት ተደራሽ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም ከተማን ለሕፃናት ምቹ ከማድረግ አንጻር አዲስ አበባ ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለአህጉሩና ለዓለም ተምሳሌት መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህም በመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የቀዳማዊ ልጅነት መድረክ ላይ በሰፊው ታይቷል ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ