አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመቐለ ከተማ የመሶብ አገልግሎት ማዕከልን ለመክፈት የትግራይ ክልል የአመራርና የቴክኒክ ባለሙያዎች ቡድን በፌዴራል መሶብ አገልግሎት ማዕከል ስልጠናና የልምድ ልውውጥ እያደረገ ነው።
ስልጠናው በመቐለ ከተማ ለመክፈት የታቀደውን የመሶብ አገልግሎት ማዕከል ውጤታማ መሆን የሚያግዝ መሆኑ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ በሚገኘው የፌዴራል መሶብ አገልግሎት ማዕከል የሚተገበሩ የሥራ ሂደቶችና የአሠራር ልምዶች ለክልሉ የአገልግሎት ዘርፍ ማገዝ የሚችልባቸው እድሎችም ተነስተዋል።
የመሶብ አገልግሎት ማዕከል የተለያዩ የመንግሥት አገልግሎቶችን በአንድ ሥፍራ በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለሕዝብ የሚያቀርብ ሥርዓት ነው።
ይህም ተገልጋዮች ከአንድ ተቋም ወደ ሌላ ሳይንከራተቱ፣ በረጅም ወረፋ ሳይጉላሉና አላስፈላጊ የወረቀት ሰነዶችን ሳያበዙ አገልግሎቶችን በቀላሉና በፍጥነት እንዲያገኙ ያስችላል።
በመቐለ የሚከፈተው ማዕከልም የመንግሥት አገልግሎቶችን የበለጠ ቀልጣፋ፣ ተደራሽና በቴክኖሎጂ የታገዘ ለማድረግ እንዲሁም የተገልጋዮችን ጊዜና ጉልበት ለመቆጠብ የሚያግዝ እርምጃ መሆኑ ተጠቁሟል።
በአሸናፊ ሽብሩ