ቢዝነስ

ኢትዮጵያ የምርቶችን ተወዳዳሪነት በማረጋገጥ አርዓያ የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወነች ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

By Hailemaryam Tegegn

November 23, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የጥራት መሠረተ ልማቶችን በአንድ ጣራ ስር በመገንባትና የምርቶችን ተወዳዳሪነት በማረጋገጥ አርዓያ የሚሆኑ ሥራዎችን እያከናወነች ነው አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፡፡

የአፍሪካ ንግድ ልማት ፎረም “የአፍሪካን የወጪ ንግድ በጥራት መገንባት” በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የዓለም ንግድ ተለዋዋጭ በሆነበት በዚህ ወቅት ወደ ገበያ ለመግባት ተፈላጊውን የጥራት ደረጃ ማሟላት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

አፍሪካ ከ1 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ወጣት ሕዝብ፣ ሰፊ መሬትና የማዕድን ሀብት ቢኖራትም፤ እሴት በመጨመር ሀብቷን ወደ ተጨባጭ አቅም ከመቀየር ይልቅ ለዘመናት ጥሬ ዕቃዎችን ብቻ በመላክ ተወስና መቆየቷን አንስተዋል፡፡

ምን ያህል ላክን ሳይሆን ምን ያህል እሴት ጨመርን የሚለው የስኬት መለኪያ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸው፤ ጥራት እምነትን ይገነባል፤ መተማመን ደግሞ የንግድ መገበያያ ገንዘብ ነው ብለዋል።

አፍሪካ በዓለም ንግድ ድርጅትና በዓለም አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ ሌሎች ያወጡትን ሕግ ተቀባይ ብቻ ሳትሆን በአንድ ድምጽ መናገር መቻል እንዳለባት አስገንዝበዋል።

በጥራት ጉድለት ምክንያት ከሀገራት ድንበር የሚመለስ እያንዳንዱ የአፍሪካ ምርት የላኪዎችን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የአህጉሪቱን ስም ያጎድፋል ነው ያሉት፡፡

ግባችን ምርቶች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበትና ከድንበራችን ባሻገር ክብር የሚያስገኝ ወጥ የሆነ አህጉራዊ የጥራት ሥርዓት መገንባት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ የደረጃዎች ምደባ፣ ፍተሻ፣ ሰርቲፊኬሽን፣ ሜትሮሎጂና አክሬዲቴሽን ተቋማትን በአንድ ጣራ ስር ያሰባሰበ ዘመናዊ የጥራት መንደር መገንባቷን ገልጸዋል።

ይህም የኢትዮጵያ ንግድ ተቋማት የማንኛውንም ዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎት እንዲያሟሉና በኢትዮጵያ የተመረተ (Made in Ethiopia) የሚለው ስም በሄደበት ሁሉ ተዓማኒነት እንዲኖረው እንደሚያስችል አብራርተዋል።

በፎረሙ ላይ ከ10 በላይ የአፍሪካ ሀገራት የንግድ ሚኒስትሮች እንዲሁም ከ300 በላይ የንግድና የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡

በአንዱዓለም ተስፋዬ