አዲስ አበባ፣ ሕዳር 14፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ታላላቅ የአሜሪካ ወደቦች እና የመርከብ ኩባንያዎች የዓለም አቀፍ ንግድና የኃይል አቅርቦት ደም ስር የሆኑ መስመሮችን ዒላማ ያደረገ ከፍተኛ የሳይበር ጥቃት እያጋጠማቸው መሆኑ ተነገረ።
አሜሪካ በቅርብ ወራት ውስጥ የወንጀል ቡድኖችና ጠላት ካለቻቸው አካላት ጋር ግንኙነት ያላቸው የኮምፒውተር መረብ ጠላፊዎች (ሀከሮች) የተራቀቀ የሳይበር ጥቃት ለመፈጸም ተደጋጋሚ ሙከራ ሰንዝረው እንደነበር ነው የተገለጸው።
በቀን 2 ነጥብ 3 ሚሊየን በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የሚያስተናግደው የቴክሳሱ የኮርፐስ ክሪስቲ ወደብ በየቀኑ በሺዎች የሚቆጠሩ የጥቃት ሙከራዎች እንደተቃጣበት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ኬንት ብሪተን ገልጸዋል።
ጠላፊዎች ራሳቸውን የኩባንያ ከፍተኛ ኃላፊዎች ማንነት በማስመሰል የማጭበርበሪያ መልዕክቶችን ከመላክ ጀምሮ መረጃዎችን ለመስረቅና ለማጥፋት ሙከራ ሲያደርጉ እንደነበር ተጠቅሷል።
ባለሙያዎች ሀገራትን በስም በመጥቀስ ከጥቃቶቹ ጀርባ እጃቸው እንዳለበት አስታውቀዋል።
የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) ጠላፊዎች አርቴክስ (Artex) በተባለ ራሱን በራሱ በሚያዝ ሰው ሰራሽ አስተውሎት ጥቃቶችን ለማቀናጀት እየተጠቀሙ መሆኑን አስጠንቅቋል።
ባለፈው ዓመት የባህር ላይ የሳይበር ጥቃቶች በ17 በመቶ ሲጨምሩ፤ የሎስ አንጀለስ ወደብ በነሐሴ ወር ብቻ 120 ሚሊየን የጥቃት ሙከራዎችን አክሽፏል ተብሏል።
እንዲሁም ግዙፉ የመርከብ ኩባንያ ማዕርስክ (Maersk) የመረጃ ምንተፋ እንደደረሰበት አስታውቋል።
ይህንን ስጋት ለመከላከል ወደቦች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎችን እየቀጠሩ እና ከአሜሪካ የባህር ጠረፍ ጥበቃ ጋር ወርሃዊ ልምምዶችን እያደረጉ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም ዲጂታል ሥርዓታቸው ቢጠቃ ሥራ እንዳይቋረጥ በሬዲዮ፣ በወረቀት መዛግብትና በእጅ ምልክቶች መርከቦችን ለመምራት የሚያስችል የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ዕቅድ ጭምር መዘጋጀቱን ፋይናንሺያል ታይምስ ዘግቧል።
ከሰሞኑ በታላላቅ የአሜሪካ ባንኮች፣ ማይክሮ ሶፍት፣ እንዲሁም አየር መንገዶች እና መንግሥታዊ ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት ተሰንዝሮ በርካታ መስተጓጎልና የአገልግሎት መቋረጥ መፈጠሩ ይታወሳል።
ለዚህ ችግር በዋናነት ሰው ሰራሽ አስተውሎት ኤጀንቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ዘገባዎች ያመላክታሉ፡፡