ቢዝነስ

በአማራ ክልል 41 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰበሰበ

By Yonas Getnet

November 24, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 15፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአማራ ክልል ከተለያዩ የገቢ ምንጮች 41 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ተሰብስቧል አለ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ።

በቢሮው የግብር ትምህርትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ታዘባቸው ጣሴ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በ2019 በጀት ዓመት 166 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል።

በዚህም እስከ ሕዳር 14 ቀን 2019 ዓም ድረስ 36 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ከመደበኛ፣ ቀሪው 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ደግሞ ከከተማ የአገልግሎት ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

የተሰበሰበው ገቢ የዓመታዊ ዕቅዱን 24 ነጥብ 8 በመቶውን የሚሸፍን መሆኑን ገልጸው አፈጻጸሙ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ15 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አንስተዋል።

አዲሱን የኤሌክትሮኒክስ ታክስ አስተዳደር ቴክኖሎጂ በመተግበር የተገኘው ይህ ለውጥ አበረታች መሆኑን እና ቴክኖሎጂዎችን የማስፋቱ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

በቀጣይም በዕቅድ የተያዘውን ገቢ በተሟላ መንገድ የመሰብሰብ ሥራ ከማስቀጠል ባለፈ የሕግ ተከባሪነትን የማረጋገጥ ተግባር በትኩረት እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በተለይም ከግብር ስወራ ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም በሚደረገው ጥረት፣ ኅብረተሰቡ ለገዛው ዕቃ ወይም ላገኘው አገልግሎት ደረሰኝ ጠይቆ በመቀበል የበኩሉን ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል።

በሌላ በኩል ከግብር አሰባሰብ ጋር ተያይዞ ከቀረቡ 87 ሺህ 903 ቅሬታዎች ውስጥ 97 በመቶ ያህሉ ምላሽ ማግኘታቸውን አመልክተው ከ26 ሺህ 954 የይግባኝ ጥያቄዎች ውስጥ 61 በመቶውን መፍታት ተችልሏ ማለታቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።