አዲስ አበባ፣ ሕዳር 16፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የማህበረሰብን ታሪክ፣ ባህል፣ እሴትና ማንነት ማንጸባረቂያ የሆነው ኪነ-ጥበብ ሕዝቦችን በጋራ እሳቤ የሚያገናኝ፣ የታሪክን የሚያጠናክርና ለማህበራዊ ለውጥ የሚያነሳሳ ኃይል አለው።
በተለይም በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኙ የሥነ-ጽሑፍ፣ የሙዚቃ፣ የሥዕል፣ የፊልም፣ የቲያትርና ሌሎች የጥበብ ውጤቶች የአፍሪካውያንን የጋራ ታሪክና ርዕይ ለማስተሳሰር ከፍተኛ ሚና አላቸው።
ፓን አፍሪካኒዝም አፍሪካውያንና የአፍሪካ ተወላጆች በታሪክ፣ በባህልና በጋራ ጥቅም የተሳሰሩ መሆናቸውን የሚያጎላ፣ አንድነትን፣ ነፃነትን፣ እኩልነትንና በራስ የመወሰን አቅምን የሚያበረታታ ሰፊ እሳቤ እንደመሆኑ ከፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትብብር ባለፈ፣ የአፍሪካን ባህላዊ ሀብት፣ ሥልጣኔ፣ ፍልስፍና የሕዝቦችን የጋራ ድምፅን ያጠናክራል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲመሰረት ጉልህ የመሪነት የተጫወተች መሆኗ ለአህጉራዊ አንድነትና ብልፅግና ላላት ታሪካዊ ሚና ማረጋገጫ ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ክስተት አዲስ አበባን የአፍሪካ አንድነትና የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ዋነኛ ማዕከል ከማድረጉም በላይ፣ የአህጉሪቱን የጋራ የነፃነት ትግል በተቋማዊ መልኩ እንዲጠናከር መሠረት ጥሏል።
ይህ ታሪካዊ ሚና በፖለቲካ ዲፕሎማሲ፣ በባህልና በኪነ-ጥበብ ዘርፍም የቀጠለ አህጉራዊ ትስስር ሲሆን ሙዚቃ፣ ሥነ-ጽሑፍ፣ ሲኒማ፣ ቲያትርና የሥዕል ጥበብ የተለያዩ የአፍሪካ ሕዝቦችን ታሪክ፣ የነፃነት ትግል፣ ባህላዊ እሴትና የወደፊት ምኞት በሚገልጽ መልኩ እንዲቃኝ ያግዛል፡፡
የዚህ እሳቤ አህጉራዊ እውቅና በአፍሪካ ሕብረት የ2063 አጀንዳ ውስጥም በግልጽ ተካትቷል። ይህም አፍሪካ ጠንካራ ባህላዊ ማንነት፣ የጋራ ቅርስና እሴቶችን የምትጋራ አህጉር እንድትሆን ግብ ያስቀምጣል።
በዚሁ ማዕቀፍ የፓን አፍሪካኒዝም እሳቤን ማጠናከር፣ የአፍሪካን ቅርስና ባህል መጠበቅ፣ ቋንቋዎችን ማሳደግና የፈጠራ ኪነ-ጥበብ ዘርፎችን ለአህጉሪቱ ዕድገት ማስተዋወቅ ዋነኛ ትኩረቶች ናቸው።
የመደመር መንግሥትም ኪነ-ጥበብን ለሀገራዊ እሴቶች ግንባታና ለአህጉራዊ አንድነት ማጠናከሪያ መሣሪያ መሆኑን ያሰምርበታል፤ በተግባርም እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡
በፓንአፍሪካኒዝም እሳቤ የተቃኙ የጥበብ ሥራዎች ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ ምቹ ሁኔታዎችን ማስፋፋት፣ የአርቲስቶችን የፈጠራ አቅም ማበረታታትና የባህል ልውውጥን ማጠናከርም የዚህ ጥረት አካል ናቸው።
የፊልም፣ የሙዚቃ፣ የፋሽን፣ የቲያትርና የሥነ-ጽሑፍ ዘርፎች የወጣቶችን የፈጠራ ክህሎት ከማሳደግ ባለፈ፣ የቱሪዝም ዘርፍን ለማነቃቃትና የሀገርን ገጽታ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ አቅሞች ናቸው።
በተለይም ትውልድ የራሱን ታሪክና ባህል እንዲያውቅ፣ የአፍሪካን የጋራ ታሪክ እንዲረዳና በፈጠራ ሥራዎቹ የአህጉሪቱን ማንነት እንዲያንጸባርቅ እና እንዲያስተዋውቅ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ የማይተካ ሚና አለው።
የተለያዩ የአፍሪካ ቋንቋዎች፣ ዜማዎች፣ ውዝዋዜዎች፣ ትውፊቶች፣ ስነ ቃሎች፣ አህጉራዊ እውቀቶች በዘመናዊ የጥበብ ሥራዎች ውስጥ ሲካተቱ ባህላዊ ሀብትን ከመጠበቅ ባለፈ ለትውልድ የሚተላለፍ የአፍሪካዊ ጋራ ትርክት ይገነባሉ።
ኢትዮጵያ በፓን አፍሪካኒዝም እሳቤ ውስጥ ያላትን ታሪካዊ ሚና በማስቀጠል የጥበብ ሥራዎችን ለሕዝብ የማድረስና የኪነጥበብ ባለሙያዎችን አቅም የማጎልበት ጥረቷን አጠናክራ ትቀጥላለች። ይህም አፍሪካዊ እሴቶችን በማስተዋወቅ ለሀገራዊ ማንነት ግንባታና ለአፍሪካዊ አንድነት የሚኖራትን አስተዋጽኦ ይበልጥ ያጎላዋል።
በምሕረት ደምሴ