የሀገር ውስጥ ዜና

ከኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ኮርፖሬሽንን የሚገኘውን ትርፍ ወደ 43 ቢሊየን ብር ማሳደግ ተችሏል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By Yonas Getnet

November 26, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ከኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ኮርፖሬሽንን የሚገኘውን ትርፍ ወደ 43 ቢሊየን ብር ማሳደግ ተችሏል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።

7ኛው የኢፌዴሪ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ እንዳሉት፤ የባቡር ኮርፖሬሽን ከዓመታት በፊት በመንግሥት የሚተዳደር አልነበረም።

የኢትዮ- ጅቡቲ ባቡር ኮርፖሬሽንን ለማሻሻል በተከናወኑ ስራዎች ከዚህ በፊት ይገኝ የነበረውን ትርፍ ከ3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወደ 43 ቢሊየን ብር ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም የኮርፖሬሽኑን አገልግሎት ማስፋትና ማሻሻል መቻሉን ገልጸው፤ 11 የነበሩት ሎኮሞቲቮች 36 ደርሰዋል ብለዋል።

560 ጋሪዎች እንደነበሩት አስታውሰው፤ አሁን ላይ ከ1 ሺህ በላይ ጋሪዎችንም ማስተዳደር ችሏል ነው ያሉት።

የመንገደኞችን አገልግሎትም ከ198 ሺህ ወደ 588 ሺህ አሳድጓል፤ ከካርጎ አንጻርም ወደ 4 ነጥብ 3 ሚሊየን ቶን ካርጎ ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል።

የባቡር የማጓጓዝ ፍጥነት ከ37 ኪሎ ሜትር በሰዓት ወደ 55 ኪሎ ሜትር ማደጉን ገልጸዋል።

ከ95 በመቶ ያላነሰ የቡና ወጪ ንግድ እንዲሁም 25 በመቶ የማዳበሪያ ገቢ ንግድ በባቡር እየተከናወነ መሆኑን አንስተው፤ አሁን ላይ ወደ 100 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ ስራዎችን በራስ አቅም እየገነባን ነው ብለዋል።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በምሕረት ደምሴ