አዲስ አበባ፣ ሕዳር 17፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አንዳንድ ቅጽበቶች ከመደበኛው የጉባኤ ሥነ ሥርዓትና ከሕግ ማርቀቅ ሒደት ባለፈ የአንድን ሀገር ሕዝብ የልብ ትርታ የሚያሳዩ መስታዎቶች ናቸው።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳራሽ ውስጥ የምክር ቤቱ አባላት ከመቀመጫቸው ተነስተው ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያሰሙት ሞቅ ያለ ጭብጨባም እንዲሁ በቀላሉ የሚታለፍ ክስተት ሳይሆን፣ የአንድ ትውልድ የውለታ ምስክርነት የታተመበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው።
በፖለቲካና በሥነ መንግሥት ባህል ውስጥ “ከመቀመጫ መነሳት” እጅግ ጥልቅ የሆነ የትሕትና እና የላቀ ክብር መገለጫ መሆኑ ይታወቃል፡፡
ሕግ አውጪዎቹ ከወንበራቸው ሲነሱ የመላው ኢትዮጵያውያን ውክልና በአንድነት ቆሞ ለሀገሩ ሕልውና ዘብ ለቆመው ሠራዊት “ክብር ይገባሃል” ማለቱ ነው።
በረሃውንና ቁሩን ታግሦ፣ የራሱን ምቾትና ሕይወት ለሀገር ሰላም አሳልፎ ለሰጠ ወታደር፣ የሕዝብ ተወካዮች በአንድ ድምፅ ያሳዩት አክብሮት ውለታው መቼም ቢሆን በታሪክ መዝገብ ላይ የማይደበዝዝ መሆኑን ያረጋግጣል።
ይህ በምክር ቤቱ አዳራሽ ውስጥ ያስተጋባው ጭብጨባ ከድምፅ ባለፈ ለግንባር ተዋጊው ትልቅ የመንፈስ ስንቅ ነው።
በወታደራዊ ሥነ ልቦና ውስጥ ከዘመናዊ ትጥቅና ስንቅ በላይ ወሳኙ ጉዳይ፣ ተዋጊው ኃይል ሕዝቡ ከጎኑ መቆሙንና የሚከፍለው መስዋዕትነት ዋጋ እንዳለው ማወቁ ነው።
በምክር ቤቱ የታየው የአብሮነት መንፈስ፣ በድንበር ላይ ለቆመው ወታደር “ብቻህን አይደለህም፤ መላው ሕዝብ ከጎንህ አለ” የሚል ጽኑ መልዕክት የሚያስተላልፍ የሞራል ኃይል ሲሆን÷ ክስተቱ በሀገራዊ ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ልዩነቶች ቦታ እንደሌላቸው በአደባባይ ያሳየም ሆኗል።
የመከላከያ ሠራዊቱ የኢትዮጵያ ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መገለጫና የሕልውናዋ ዋስትና እንደመሆኑ መጠን በምክር ቤቱ የተሰጠው ክብር ሀገርን የማጽናት ጉዞ በሕዝብና በሠራዊቱ የማይበጠስ ትስስር እንደሚቀጥል ያመላክታል፡፡
በምክር ቤቱ አዳራሽ የተሰማው ጭብጨባ ፣ ትርጉሙ ግን በትውልድ ልብ ውስጥ ታትሞ ይኖራል። ዳር ድንበርን እያስከበረ ለሚገኘው ጀግና ሠራዊት የተሰጠው ይህ ክብር ሀገር በልጆቿ መስዋዕትነት ጸንታ እንደምትኖርና ባለውለታዎቿን የምታከብር ታላቅ ሀገር መሆኗን በድጋሚ ያስመሰከረ የታሪክ ምዕራፍ ነው።
በኃይለኢየሱስ መኮንን