መቀመጫውን በዱባይ ያደረገው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ያንጎ ግሩፕ፣ ከአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣንና ሴቭ ዘ ኔሽን ጋር በመተባበር፣ በመላው አፍሪካ እየተተገበረ ያለውን የያንጎ ፓን አፍሪካ “ደኅንነቱ የተጠበቀ የትምህርት ቤት ጉዞ” የተሰኘውን ተነሣሽነት በኢትዮጵያ በይፋ አስጀምሯል።
መርሐ ግብሩ በአዲስ አበባ በሚገኙ 4 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ12,500 በላይ የሚሆኑ ተማሪዎችን ተግባራዊ የመንገድ ደኅንነት ትምህርት በመስጠትና በትምህርት ቤቶቹ አካባቢ፣ የመንገድ ደኅንነትን የሚያጠናክሩ የመሠረተ ልማት ማሻሻያዎችን በማከናወን የተማሪዎችን የጉዞ ደኅንነት ለማሻሻል ያለመ ነው።
ተነሣሽነቱ፣ ሕጻናት በትራፊክ ፍሰት ውስጥ ደኅንነታቸው ተጠብቆ እንዲንቀሳቀሱ ለማገዝ፣ ለ25 ቀናት የሚቆይ የመንገድ ደኅንነት ሥልጠናን ሰጥቷል።
በፕሮግራሙ ተሳታፊ ከሆኑት ትምህርት ቤቶች ደግሞ፣ በሁለቱ የአካባቢ መንገድ ደኅንነት ሁኔታ ግምገማ ተካሂዶ፣ በዚሁ መሠረት የእግረኞች መሻገሪያዎችን፣ የፍጥነት መቀነሻ ጉብታዎችን፣ የፍጥነት ገደብ ምልክቶችን እና መከላከያ አጥሮችን ጨምሮ የመሠረተ ልማት ማሻሻያዎችን አድርጓል።
ፕሮግራሙ፣ የትምህርት ሥልጠናን በትምህርት ቤቶች አካባቢ ከሚደረጉ ተጨባጭ የመንገድ ማሻሻያዎች ጋር በማቀናጀት፣ ሕጻናት በየዕለቱ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱም ሆነ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ለአደጋ ሊያጋልጧቸው የሚችሉ ሥጋቶችን ለመቀነስ ያለመ ነው።
በመርሐ ግብሩ መንግሥት መሰል ተነሣሽነቶችን እንደሚደግፍ የተገለጸ ሲሆን÷ ለሥልጠናው እና የመንገድ ደኅንነት ማሻሻያ ሥራው ስኬታማ ትግበራ ላበረከቱ ለያንጎና ሁሉም አጋር አካላት ምስጋና ቀርቧል፡፡
“በትምህርት ቤቶች አካባቢ የመንገድ ደኅንነትን ማረጋገጥ የመንግሥት፣ የአጋር አካላት፣ የትምህርት ቤቶችና የቤተሰቦች የጋራ ኃላፊነት ነው። ይህ የሥልጠና መርሐ ግብር ለተማሪዎች የሚሰጥ ተግባራዊ ሥልጠናን በመንገድ ላይ ከሚታዩ ተጨባጭ የደኅንነት ማሻሻያዎች ጋር ያቀናጀ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
የያንጎ፣ የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር የቀናለም አበበ ደኅንነቱ የተጠበቀ የትምህርት ቤት ጉዞ” የተሰኘው ተነሣሽነት፣ ይህንን አሠራር በተግባር የምናሳይበት አንዱ ምሳሌ ነው፤ ከአካባቢው አጋር አካላት ጋር በመተባበር፣ ሕጻናት በየዕለቱ ወደትምህርት ቤት በሚያደርጉት ጉዞ የበለጠ በራስ መተማመን እንዲኖራቸውና በደኅንነት እንዲንቀሳቀሱ ለማገዝ እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
እንደዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ሪፖርት፣ በየዓመቱ ከ21,000 በላይ ሰዎች በኢትዮጵያ በመንገድ አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ይገመታል።
ሴቭ ዘ ኔሽን የተቋቋመው በት/ቤቶች አካባቢ ያሉ መንገዶችን ለሕጻናት ደኅንነታቸው የተጠበቀ ለማድረግ ሲሆን ÷ከያንጎ እና ከትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ጋር በመተባበር፣ ተማሪዎች በክፍል ውስጥ የመንገድ ደኅንነት ሕጎችን እንዲገነዘቡ ከማድረጉ ባሻገር፣ በሁለት ት/ቤቶች እነዚህን ሕጎች በተግባር ሲተገበሩ ለማሳየት በመንገድ ላይ በተዘጋጁ የእግረኛ መሻገሪያዎች፣ የትራፊክ ምልክቶችና መከላከያ አጥሮች ላይ ማሻሻያዎችን ማድረግ ችሏል።