ቢዝነስ

በገቢዎች ቢሮ ስም በማጭበርበር የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Yonas Getnet

November 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የገቢዎች ቢሮ ሠራተኞች ነን በሚል ሐሰተኛ ማንነት የንግድ ተቋማትን በማጭበርበር የተጠረጠሩ ሁለት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በቱሉ ዲምቱ ወረዳ በሚገኙ የንግድ ተቋማት በመዘዋወር፣ ነጋዴዎች ያለደረሰኝ ግብይት ፈጽመዋል በሚል 100 ሺህ ብር ቅጣት እንደሚጣልባቸው በማስፈራራት እና 50 ሺህ ብር ለእነሱ እንዲከፍሉ በመጠየቅ ሲያጭበረብሩ እንደነበር ተገልጿል።

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሕግ ተገዢነት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ፓርቲ ንጉሴ፣ ተጠርጣሪዎቹ ሐሰተኛ መታወቂያዎችን በማዘጋጀት የማጭበርበር ወንጀሉን ሲፈጽሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ተጠርጣሪዎቹ አቶ ምትኩ ጋዲሰ በሐሰተኛ ስም አየለ ጥላሁን፣ እንዲሁም አቶ ጌታሁን ደቻሳ በሐሰተኛ ስም አድማሱ ከበደ በሚል ማንነታቸውን በመቀየር የሐሰት መታወቂያዎችን ተጠቅመው ሲያጭበረብሩ መቆየታቸውን እና ከንግዱ ማኅበረሰብ በተሰጠ ጥቆማም ተጠርጣሪዎቹ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አስረድተዋል።

በአሁኑ ወቅት በተጠርጣሪዎቹ ላይ በሕግ አግባብ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን የገለጹት አቶ ፓርቲ፣ በእጃቸው የገቢዎች ቢሮ ሠራተኛ መሆናቸውን ከሚያሳይ ሐሰተኛ መታወቂያ በተጨማሪ የመሬት ባለሙያ መሆናቸውን የሚገልጽ ሌላ ሐሰተኛ መታወቂያም መገኘቱን ጠቁመዋል።

ከዩኒፎርም ውጭ የቁጥጥር ሥራ የሚያከናውኑ የገቢዎች ቢሮ ሠራተኞች ባርኮድ ያለው መታወቂያ የሚይዙ መሆኑን በማስታወስ፣ ግብር ከፋዮች የቢሮውን ሠራተኞች መታወቂያ በመጠየቅና ባርኮዱን በስልካቸው ስካን በማድረግ ትክክለኛ ማንነታቸውን እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።

በተጨማሪም የንግዱ ማኅበረሰብ በገቢዎች ቢሮ ስም የሚፈጸሙ መሰል የማጭበርበር ድርጊቶች ሲያጋጥሙት ለፀጥታ አካላት ወይም ቢሮው ባዘጋጀው 7075 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።