የሀገር ውስጥ ዜና

በመቐለ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስጀመር የሚደረገው ዝግጅት ተጠናክሮ ይቀጥላል – አገልግሎቱ

By tigist gizachew

November 27, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በመቐለ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስጀመር የሚደረገው ዝግጅት ተጠናክሮ ይቀጥላል አለ የፌደራል የመሶብ አገልግሎት፡፡

በትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የመቐለ ከተማ አስተዳደር ከፌደራል የመሶብ አገልግሎት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሰረት በከተማዋ የመሶብ አገልግሎትን ለማስጀመር በአዲስ አበባ ሲሰጥ የቆየው ስልጠና ተጠናቅቋል፡፡

የፌደራል የመሶብ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ አለማየሁ የስልጠናውን መጠናቀቅ ተከትሎ ከሰልጣኝ ቡድኑ አባላት ጋር በቀጣይ ስራዎች ዙሪያ ተወያይተዋል።

ከአመራርና ባለሙያዎች የተወጣጣው ቡድኑ የመስክ ምልከታን ያካተተ የአቅም ግንባታ ስልጠና ሲከታት የቆየ ሲሆን፤ ቡድኑ ወደ መቐለ በመመለስ አገልግሎት ለማስጀመር እየተደረገ ያለውን ዝግጅት አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

በከተማዋ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ለማስጀመር እየተደረገ የሚገኘው ዝግጅት አገልግሎቱን ወደ ሌሎች የክልሉ ከተሞች ለማስፋት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተመላክቷል።