አዲስ አበባ፣ ሕዳር 18፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) አፍሪካ የጤና ሉዓላዊነቷን በራሷ አቅም፣ በተቀናጀ ሥርዓትና በዘላቂ የጤና ፋይናንስ ማረጋገጥ ይገባታል አሉ የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ።
“የአፍሪካ የጤና ደኅንነትና ሉዓላዊነት፤ ከጤና ጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት የሚደረግ ሽግግር” በሚል መሪ ሀሳብ ከሕዳር 14 ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሄድ የቆየው 5ኛው ዓለም አቀፍ የአፍሪካ የሕዝብ ጤና ጉባኤ ተጠናቅቋል።
ሚኒስትሯ በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት ቀናት በተካሄዱ ከ90 በላይ የውይይት መድረኮች የሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎች እንዲሁም የግሉ ዘርፍ ተወካዮችና የሲቪል ማኅበራት ተሳትፈዋል።
በዚህም አፍሪካ በአንድ ድምፅ መናገር መቻሏንና ከጥገኝነትና ተጋላጭነት ወደ ባለቤትነትና ጽናት መሸጋገር የመላው አህጉሪቱ የጋራ ግብ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የተሳታፊዎች ድምፅ ግልጽና ጠንካራ እንደነበር የጠቆሙት ሚኒስትሯ፣ ይህም ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ በተግባር እየተከተለችው ያለው አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍና በወረርሽኞች ዝግጁነት ረገድ በቁርጠኝነት እየሠራች መሆኗን ገልጸው፣ ባለፉት ዓመታት ያገኘችውን ልምድ ለአፍሪካ ሀገራት ለማካፈል ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።
የአፍሪካ ጤና በአፍሪካውያን መመራት፣ በአፍሪካውያን መደጎምና በአፍሪካውያን ጥረት መንቀሳቀስ እንዳለበት መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡