ቴክ

የሳይበር ደህንነትንና ዲጂታል ሥነ ምግባርን ከትምህርት ሥርዓቱ ጋር ማቀናጀት ወሳኝ ነው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

By Yonas Getnet

November 28, 2026

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን በብቃት መወጣት የሚችል ትውልድ ለማፍራት የሳይበር ደህንነትንና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን ከትምህርት ሥርዓቱ ጋር ማቀናጀት ይገባል አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር በ5ኛ ዙር ሀገር አቀፍ የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ቻሌንጅ ያሰለጠናቸውን ሰልጣኞች አስመርቋል።

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በዚህ ወቅት ዓለም በ4ኛው የኢንዱስትሪ አብዮት ውስጥ እየተሻገረች መሆኗን ገልጸው÷ የሰው ልጅ የሥራ፣ የመማር፣ የማምረትና የመገናኘት ሁኔታዎች በቴክኖሎጂ እየተቀየሩ እንደሚገኙ አስረድተዋል።

በተለይም የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጂዎችና ሌሎች ዘመናዊ ፈጠራዎች በሁሉም ዘርፎች እያመጡት ያለው ለውጥ የትምህርት ሥርዓቱ ከዘመኑ ጋር እንዲራመድ ግድ እንደሚል ጠቁመዋል።

የትምህርት ሥርዓቱ የተማሪዎችን የንድፈ ሐሳብ ዕውቀት ከማሳደግ ባለፈ በተግባር የመሥራት፣ የመፍጠር፣ ችግርን የመፍታትና በማስረጃ ላይ ተመሥርቶ የማሰብ ክህሎቶችን ማዳበር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በተለይም የሳይንስ፣ የቴክኖሎጂ፣ የምሕንድስናና የሒሳብ ትምህርቶችን ማጠናከር፣ የተማሪዎችን በጥልቀት የማሰብ አቅም ማሳደግና የፈጠራ ችሎታቸውን ማበረታታት ለዘመኑ የሚመጥን የሰው ኃይል ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ከመሠረታዊ የቴክኖሎጂ ክህሎት ባለፈ የሥነ ምግባር፣ የኃላፊነትና የደህንነት ጉዳይ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በዲጂታል ዓለም የሚኖሩ ተጠቃሚዎች ቴክኖሎጂን በአግባቡና በኃላፊነት መጠቀም፣ የመረጃ ደህንነታቸውን መጠበቅና የሳይበር ስጋቶችን መለየት እንዲችሉ ከታችኛው የትምህርት እርከን ጀምሮ ማስተማር እንደሚገባ አብራርተዋል።

የሀገርን የዲጂታል መሠረተ ልማት መጠበቅ፣ የቴክኖሎጂ አቅምን ማሳደግና የዲጂታል ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ በዕውቀት፣ በክህሎትና በኃላፊነት የተገነባ ትውልድ መፍጠርን እንደሚጠይቅ መናገራቸውንም የኢመደአ መረጃ ያመላክታል፡፡