አዲስ አበባ፣ ሕዳር 19፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በዛሬው ዕለት 92 የሕክምና ዶክተሮችን አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከልም 36ቱ ሴቶች ናቸው፡፡
ዶክተር እጹብ ስንታየሁ ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጅ 3 ነጥብ 86 በማምጣት የሜዳሊያ ተሸላሚ ሆናለች፡፡
ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበችው ዶ/ር እጹብ ስንታየሁ ውጤቱ በሕይወቴ ትልቅ ትርጉም ፈጥሮ ሕይወት ለማዳን አዘጋጅቶኛል ብላለች፡፡
ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የልፋቴን ዋጋ በማግኘቴ ትልቅ ደስታ ተሰምቶኛል ነው ያለችው።
የተማርንበት ሙያ ሰውን በማገልገል እና በማከም ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ሕዝባችንን በማገልገል የሀገራችንን እና የሕዝባችንን አደራ ለመወጣት ቁርጠኞች ነን ብላለች።
ለኢትዮጵያ የሕክምና ዘርፍ አዲስ ዕውቀትና አቅም ይዛ ወደ ሥራው ዓለም በመሰማራት የተሻለ ነገር ለማበርከት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች፡፡
ባለፈው ዓመት የዩኒቨርሲቲው የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ከፍተኛው ውጤት በሴት ተማሪ የተመዘገበ ሲሆን÷ ዘንድሮም ዶ/ር እጹብም የዩኒቨርሲቲውን የሴት ተማሪዎች ስኬት ማስቀጠል ችላለች፡፡