አዲስ አበባ፣ ሕዳር 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የትግራይ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት መመሥረት ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ መንገድ በውይይት ለመፍታት እገዛ ያደርጋል አለ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ም/ቤት፡፡
በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ 19 የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈ የትግራይ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በይፋ ተመሥርቷል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ሉዓላዊነትና በብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች ላይ በጋራ ሊሰሩ ይገባል፡፡
የክልሉ የጋራ ምክር ቤት መመሥረት የፖለቲካ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በሰለጠነ መንገድ በውይይት እንዲፈቱ ትልቅ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ቢኖራቸውም በሀገር ሉዓላዊነት፣ በዘላቂ ሰላም፣ በብሔራዊ ጥቅምና በመልሶ ግንባታ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በትግራይ ክልል የሚካሄደው ምርጫ ሰላማዊና ተዓማኒ እንዲሆን እንዲሁም ተፈናቃይ ወገኖች ወደ ቀዬአቸው እንዲመለሱ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል። ብሔራዊው የጋራ ምክር ቤት ለትግራይ ክልል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስፈላጊውን ተቋማዊ ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ነዋይ በበኩላቸው፤ ቦርዱ በክልሉ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ሙያዊና አካታች የሆነ ጠቅላላ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አዲሱ ምክር ቤት የምርጫ ሕጎችንና ነጻነቱን ጠብቆ በመንቀሳቀስ በፓርቲዎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት ለመፍታት መስራት ይጠበቅበታል ነው ያሉት፡፡ በቀጣይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ተከታታይ ውይይቶች እንደሚደረጉ አመልክተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች በመተዳደሪያ ደንባቸው መሠረት ዕጩዎችን እንዲመለምሉና ሕዝቡን ለምርጫ እንዲያዘጋጁ ጠይቀው፤ የመንግሥት አካላት በምርጫው ለሚወዳደሩ ፓርቲዎችና እጩዎች ፍትሐዊ የመወዳደሪያ ሜዳ እንዲፈጥሩ አሳስበዋል።
በአሸናፊ ሽብሩ