የሀገር ውስጥ ዜና

ጳጉሜን 3 የአምባሳደርነት ቀን በተለያየ መርሃ ግብር እየታሰበ ነው

By Meseret Demissu

September 08, 2020

አዲስ አበባ ፣ጳጉሜን 3 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ጳጉሜን 3 የአምባሳደርነት ቀን “እኔም የከተማዬ አምባሳደር ነኝ “በሚል መሪ ሃሳብ በተለያየ መርሃ ግብር እየታሰበ ነው።

መርሃ ግብሩ ከማለዳው ጀምሮ የአስተዳደሩ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ዣንጥራር አባይ በተገኙበት መከናወኑ ተገልጿል።

በመንገድ ጽዳት ሥራ ለተሰማሩና ለበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የአዲስ ዓመት በዓል ስጦታ በማበርከት የእለቱ መርሃ ግብር ተጀምሯል።

ዕለቱን በማስመልከትም መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በአረንጓዴ አሻራ የተከሏቸውን ችግኞች እንክብካቤ አድርገዋል።

አቶ ዣንጥራር አባይ ስጦታውን ካበረከቱ በኋላ ባደረጉት ንግግር ከተማዋን ውብና አረንጓዴ ለማድረግ ለሚተጉት የጽዳት ሰራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።

የጽዳት ዘመቻው የክፍለ ከተማ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ መደበኛ የጽዳት ሰራተኞች በተገኙበት አምባሳደር ቲያትር ቤት አካባቢ ተከናውኗል።

በቀጣዩ ዓመት የመዲናዋን የጽዳት ሥራ እንደ አንድ ዋነኛ የመንግሥት ተግባር አድርገን የምንሰራው ይሆናልም ነው ያሉት።

የጽዳት ዘመቻ የአንድ ወቅት ሥራ ብቻ ሳይሆን የዕለት ተዕለት ተግባራችን ልናደርገው ይገባል ሲሉም ምክትል ከንቲባው አሳስበዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።

የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ በፌስ ቡክ ገጻቸው ላይ÷ በከተማችን ያላችሁ “እኔ ለሃገሬ አምባሳደር ነኝ” ብላችሁ አመቱን ሙሉ በሁሉም ክ/ከተሞች እና ወረዳዎች ፀሃይ፣ ብርድ እና ዝናብ ሳያሰለቻችሁ የከተማችንን ውበት እና ጽዳት ስታቀናጁ እና ስትጠብቁ የከረማችሁ፣ ስለድካማችሁ ሁሉ ከልቤ አመሰግናለሁ ብለዋል።

ሁላችንም አካባቢያችንን እንደምናጸዳ ውስጣችንንም ከቂም፣ ከጥላቻ እና ከበቀል ንጹህ እናድርግ ብለዋል ።

ምክትል ከንቲባዋ አያይዘውም ዛሬ በመዲናዋ ያሉ የአለማቀፍ እና ዲፕሎማሲያዊ ማህበረሰብ ከዚህ ቀደም የተከሏቸውን ችግኞች በዛሬው ዕለት እንከብካቤ  በማድረጋቸው ምስጋናዬ የላቀ ነው ብለዋል።

አዲስ አበባ ከዓለም የዲፕሎማሲ ማዕከላት አንዷከመሆኗም ባለፈ የበርካታ ሀገራት፣ የአህጉራዊና ዓለም አቀፍ አምባሳደሮች መኖሪያም ናት  ሲሉ ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባን መኖሪያቸው ያደረጓት ሁሉ አምባሳደሮቿ ናቸው ሲሉም ወይዘሮ አዳነች  ገልጸዋል ።