የሀገር ውስጥ ዜና

በ2013 በሀገር አቀፍ ደረጃ የኤሌክትሪክ የሀይል ተደራሽነት ለማሳደግ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለፀ

By Tibebu Kebede

September 08, 2020

አዲስ አበባ ፣ጳጉሜን 3 ፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በ2013 አዲስ ዓመት በተለያዩ ዘርፎች ሰፊ ስራዎችን በማከናወን በሀገር አቀፍ ደረጃ የሀይል ተደራሽነትን ለማሳደግና የአገልግሎት ኔትዎርክን ለማዘመን እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ በአዲስ አበባ ብቻ በሶስት ዙር ለሚከናወነው የሀይል ማሰተላለፊያ መስመር ማሻሻል እና መቀየር ስራም 8 ቢሊየን ብር ወጪ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ የሀይል ማስተላለፊያ መስመሮችን የማሻሻል ስራ የመጀመሪያው ዙር መጠናቀቁን የተናገሩት አቶ ሽፈራው፥ ሁለተኛው እና ሶስተኛው ዙር የማሻሻል እና የማዘመን ስራም በአዲሱ ዓመት ይጀመራለም ብለዋል።

በሌሎች 6 ከተሞችም የማሻሻያ እና የማዘመን ስራም በ2013 የሚከናወን መሆኑንም ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው አቶ ሽፈራው የተናገሩት።

ከዚህ በተጨማሪ በብርሀን ለሁሉም መርሀግብር ግንባታ እየተከወነባቸው የሚገኙ 12 ከተሞች እስከ ህዳር ወር ድረስ ወደ ስራ ይገባል ያሉ ሲሆን፥ በከተሞቹም 70 ሺህ ሰዎች ተጠቃሚ ይሆናሉም ብለዋል።

እንዲሁም በአዲሱ ዓመት በመርሀ ግብሩ 25 ከተሞች ወደ ግንባታ ይገባሉ የተባለ ሲሆን፥ 1 ሚሊየን አዳዲስ ደንበኞችንም የአገልገሎቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው።

አገልግሎቱ ከአዲስ አመት ጋር ተያይዞም የሀይል መቆራረጥ እንዳይኖር የቅድመ ዝግጅት ስራ ማከናወኑንም አስታውቋል።

በዙፋን ካሳሁን