አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና ቀዳማዊ እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው ተነገረ፡፡
ይህን ተከትሎም ፕሬዚዳንቱና ባለቤታቸው በለይቶ ማቆያ ውስጥ ናቸው ተብሏል፡፡
ይህ የተሰማው የቅርብ ረዳታቸው የሆነ ሰው በኮሮና ቫይረስ መያዙ ከተነገረ በኋላ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ከትናንት በስቲያ ከጆ ባይደን ጋር ባደረጉት ፕሬዚዳንታዊ ክርክር ወቅት የቅርብ ረዳታቸው አብራቸው ነበረች ተብሏል፡፡
እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው በወቅቱ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አለማድረጋቸውም ተነግሯል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በቫይረሱ መያዛቸውን አስመልክቶ በትዊተር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት ወደ ለይቶ ማቆያ መግባታቸውን በመጥቀስ ይህንን ወቅት አብረን እናልፈዋለን ብለዋል፡፡
የፕሬዚዳንቱ ሐኪም እንደገለጹት ከሆነ በአሁኑ ወቅት ሁለቱም በመልካም ጤንነት ላይ ይገኛሉ፡፡
በኋይት ሐውስ ውስጥም ራሳቸውን አግለው እንደሚቀመጡም ነው የተናገሩት፡፡
ጥቅምት 5 ቀን ሁለተኛ ፕሬዚዳንታዊ ክርክር ከጆ ባይደን ጋር የሚጠብቃቸው ትራምፕ በቫይረሱ መያዛቸው ምን ይዞ እንደሚመጣ እስካሁን ግልጽ አይደለም ተብሏል፡፡
በተቀናቃኛቸው ጆ ባይደንና በእርሳቸው መካከል የሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ 32 ቀናት ብቻ ቀርተውታል፡፡
ምንጭ፡-ቢቢሲ