የሀገር ውስጥ ዜና

በለይቶ ማቆያነት ሲያገለግሉ የነበሩ ትምህርት ቤቶች የኬሚካል ርጭት ሳይደረግላቸው ትምህርት አይጀምሩም – ትምህርት ሚኒስቴር

By Abrham Fekede

October 05, 2020

አዲስ አበባ ፣መስከረም 25 ፣2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) ትምህርት ሚኒስቴር በለይቶ ማቆያነት ሲያገለግሉ የነበሩ ትምህርት ቤቶች የኬሚካል ርጭት ሳይደረግላቸው ትምህርት እንደማይጀምሩ አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ የተቋማቸውን የሶስት ወራት የስራ አፈጻፀም በተመለከተ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በዚህም የኮቪድ 19 ወረሽኝን በመከላከል የመማር ማስተማር ስራውን ለማስጀመር የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን አብራርተዋል።

መንግስት ለተማሪዎች የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል የማቅረብ ስራ እየሰራ መሆኑንና ትምህርት ሲጀመር ማስክ ያላደረገ ማንኛውም ተማሪ ወደ ትምህርት ቤት እንደማይገባ ተናግረዋል።

የኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ለኮሮና ቫይረስ ህሙማን ማቆያ ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ ትምህርት ቤቶችም የኬሚካል ርጭት ሳይደረግላቸው ትምህርት እንደማይጀምሩም ነው የተናገሩት፡፡

የኬሚካል ርጭቱን ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን እና በቀጣይ ሳምንታት እንደሚጀመርም ገልጸዋል፡፡

ይህንን አስቸጋሪ ወቅት በድል ለመወጣት መምህራንና ወላጆች ርብርብ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡