የሀገር ውስጥ ዜና

የኢፌዴሪ የፖሊስ ዶክትሪን ይፋ ሆነ

By Tibebu Kebede

October 09, 2020

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ የፖሊስ ዶክትሪን ዛሬ በሸራተን አዲስ ይፋ ሆነ፡፡

ዶክትሪኑ ላለፉት ሁለት ዓመታት በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን እና በሰላም ሚኒስቴር ሲዘጋጅ የቆየ ነው ተብሏል።

የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ፖሊስ የሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ጠባቂ አካል መሆኑን በተግባር ማረጋገጥ፣ ለሥርዓት ሳይሆን ለሕዝብ የሚያገለግል፣ ከፖለቲካ ነፃ የሆነ ሥርዓት ሲቀያየር የማይናወጥ ለሕዝብ የወገነ ሊሆን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

አያይዘው ፖሊስ በሕዝብ የሚፈራ ሳይሆን የሚፈለግ እንዲሆን ዶክትሪኑ አስፈልጓልም ነው ያሉት።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው ዶክትሪኑ ይስተዋሉ የነበሩ የፖሊስ ድክመቶችን ለመፍታት፣ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ የሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ለመጠበቅ የሚችል ዘመናዊና ዘመን ተሻጋሪ ፖሊስን ለመገንባት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።