የሀገር ውስጥ ዜና

ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል ተብለው ተለዩ

By Abrham Fekede

October 09, 2020

አዲስ አበባ፣ መስከረም 29፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ ስምንት የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የምርምር ልህቀት ማዕከል በመባል መለየታቸውን የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ የተመረጡት ዩኒቨርስቲዎች አዲስ አበባ፣ ጎንደር፣ ባህርዳር፣ መቐለ፣ ጅማ፣ ሃዋሳ፣ አርባምንጭና ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው።

ሚኒስቴሩ ይህንን ያስታወቀው የጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተመረጡ ትምህርት ቤቶች በትምህርት ጥራት ዙሪያ ባካሄደው የምርምር ግኝት ላይ ትናንት ከባለድርሻ አካላት ጋር በተወያየበት ወቅት ነው ተብሏል።

በወቅቱ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከፍተኛ አማካሪ ዶክተር ወርቁ ነጋሽ እንደገለጹት በሃገሪቱ የሚገኙ 46 ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በአጠቃላይ ትምህርት በሚል በሶስት ደረጃዎች ተለይተዋል፡፡

ባለፉት ዓመታት በርካታ ችግር ፈቺ የምርምር ውጤቶችን ሲያበረክቱ የቆዩና ወደፊትም አስተዋጽዖ ይኖራቸዋል የተባሉ ስምንት ዩኒቨርሲቲዎች በምርምር ዘርፍ የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ መለየታቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ለአንድ ሀገር ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ችግር ፈቺ ምርምር ቁልፍ ሚና እንዳለው የገለጹት ዶክተር ወርቁ ያደጉ ሃገራት የእድገት ሚስጥርም ከዚህ የመነጨ ነው ብለዋል፡፡

የምርምር ዩኒቨርሲቲዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አቻ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ አቅማቸውን ለመገንባት በትኩረት እንደሚሰራም አመላክተዋል፡፡

ሌሎች 15 የመንግሰት ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ መለየታቸውን ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲዎቹ በቂ እውቀትና ክህሎት ያዳበረ ዜጋ ማፍራት እንዲችሉ ተከታታይ ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አመላክተዋል።

ቀሪዎቹ 23 ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ አጠቃላይ ትምህርትና ስልጠና እንዲሰጡ የተለዩ መሆኑን ዶክተር ወርቁ ማስታወቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።