አዲስ አበባ ፣ መስከረም 30 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን ለውጥ አደንቃለሁ፤ እደግፋለሁ” በሚል መሪ ቃል በቦሌ እና የካ ክፍለ ከተሞች የፅዳት ዘመቻ ተካሄደ፡፡
በዛሬው ዕለት ማለዳ 12 ሰዓት ከ30 ጀምሮ የካ እና በቦሌ ክፍለ ከተሞች “የኢትዮጵያን ለውጥ አደንቃለሁ፤ እደግፋለሁ” በሚል መሪ ቃል የፅዳት ዘመቻ መርሃግብር መካሄዱን ከአዲስ አበባ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
በየካ ክፍለ ከተማ በተካሄደ የፅዳት ዘመቻ “የተገነባች እንጂ የፈረሰች ሀገር ለትውልድ አናስተላልፍም” በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከለውጡ አመራር ጎን በመቆም የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በማጠናቀቅ እና የኢትዮጵያን ለውጥ ወደፊት በማስቀጠል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡
በተመሳሳይም በቦሌ ክፍለ ከተማ “የሀገሬን ለውጥ አደንቃለሁ” ዐቢይ ይምራ!፣”ሁላችንም ከለውጡ አመራር ጎን ነን” እና “ከመስከረም 30 በኋላ ጥቅምት አንድ ነው”በሚሉ መሪ ቃሎች የጽዳት ዘመቻ እና ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የድጋፍ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡