የሀገር ውስጥ ዜና

13ኛው የሰንደቅ አላማ ቀን ተከበረ

By Tibebu Kebede

October 12, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 13ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን ለሰላማችን፣ ለአብሮነታችንና ለሃገራዊ ብልጽግናችን!” በሚል መሪ ቃል ተከበረ።

ቀኑ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሪነት በፌደራል፣ በክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደር ከተሞች የተከበረው።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቅጥር ግቢም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መአዛ አሸናፊ፣ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲ ተጠሪዎች በተገኙበት ተከብሯል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፥ በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ኩራትን፣ ክብርን እንዲሁም ከፍተኛ የሀገር ስሜትን በአንድ ላይ ከሚይዙ ጥቂት ጉዳዮች መካከል ሰንደቅ አላማ ዋነኛው ነው ብለዋል።

ሰንደቅ አላማ የአንድ ሀገር ነፃነት፣ ሉአላዊነት እንዲሁም ህገ መንግስታዊነት ማረጋገጫ ነው ሲሉም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ተናግረዋል።

“ሰንደቅ አላማ ከሌሎች ጋር አንድ እና እኩል መሆንን እንዲሁም የአንድ ስብስብ አካል መሆንን የሚያረጋግጥ እና አንደኛውን ከአንደኛው ጋር የሚያስተሳስር ጠንካራ ምልክት ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ረጅም የሰንደቅ አላማ ታሪክ ካላቸው ሀገራት ተርታ የምትቆጠር መሆኗን በማንሳት፤ “ከነፃ ሀገራት ተርታ እንድትቀመጥ ያስቻለን ነው” ሲሉም ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ የሚናገረው ታሪክም ኢትዮጵያውያን ዛሬ በዓለም መድረክ አንገታቸውን ቀና አድርገው የሚጓዙት ለዚህ ሰንደቅ አላማ በከተፈለው ከፍተኛ መስዋዕትነት መሆኑንም አንስተዋል።

ወቅቱ ኢትዮጵያ ከየትኛውም ወቅት ይበልጥ የሁሉንም ቀና አስተዋፅኦ በእጅጉ የምትሻበት ጊዜ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ በሰንደቅ አላማው ስር የተሰባሰቡት ልጆቿ ሳይጓደሉ ሁሉም በአንድነት እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ በበኩላቸው፥ የዘንድሮው የሰንደቅ አላማ ቀን በለውጥ ምዕራፍ ወቅት ላይ የሚከበር መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ምዕራፍም የጋራ ሰንደቅ አላማን ከፍ ለማድረግ የተመቸ እድል ተፈጥሯል ነው ያሉት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ።

መንግስትም የተጀመረውን ለውጥ ለማስጠልና ሰንደቅ አላማን ከፍ አድርጎ ለማስኬድ የህግ የበላይነትን ማስከበር አጠናክሮ ያስቀጥላልም ነው ያሉት።

የብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በተሻሻለው በሰንደቅ ዓላማ አዋጅ ቁጥር 863/2006 ዓ/ም አንቀጽ 2 መሰረት በየዓመቱ ጥቅምት ወር በገባ በመጀመሪያው ሳምንት ሰኞ እንዲከበር መደንገጉ ይታወሳል፡፡