አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 2፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) አቶ ልደቱ አያሌው በተከሰሱበት ህገመንግስቱን ለመናድ በማሰብ የተለያዩ ህገመንግስቱን የሚቃረኑ የሽግግር ሰነዶችን በማዘጋጀት ወንጀል ክስን በችሎት ለማንበብ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጠ።
አቶ ልደቱ ዛሬ ረፋድ በኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምስራቅ ምድብ ችሎት ቀርበዋል።
አቶ ልደቱ በተከሰሱበት በ1996 የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 238 ንኡስ አንቀጽ 1 እና 256 በመተላለፍ ህገመንግስቱን ለመናድ በማሰብ የተለያዩ ህገመንግስቱን የሚቃረኑ የሽግግር ሰነዶችን በማዘጋጀት ወንጀል ክስን በችሎት ለማንበብ ነበር ለዛሬ ቀጠሮ የተሰጠው።
ይሁንና አቶ ልደቱ ዛሬ ጠበቆቼ ባለመገኘታቸው ጠበቆቼ ባሉበት ተማክሬ ይነበብልኝ ማለታቸውን ተከትሎ ክሱን በችሎት በንባብ ለማሰማት ለፊታችን አርብ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ልደቱ አያሌው ከዚህ በፊት በተከሰሱበት ህገ ወጥ ጦር መሳሪያ ይዞ መገኘት ወንጀል ለነገ ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱ ይታወሳል።
ባሳለፍነው ሃሙስ ህገመንግስቱን ለመናድ በማሰብ የተለያዩ ህገመንግስቱን የሚቃረኑ የሽግግር ሰነዶችን በማዘጋጀት ወንጀል ክስ መመስረቱን መዘገባችን የሚታወስ ነው፡፡
በታሪክ አዱኛ