የሀገር ውስጥ ዜና

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በመተከል ዞን የተፈጸመውን ድርጊት አወገዙ

By Tibebu Kebede

October 12, 2020

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በመተከል ዞን በተደጋጋሚ በሚከሰተው የፀጥታ ችግር የዜጎች ህይወት መጥፋት አሳዛኝ እና ልብ ሰባሪ ድርጊት መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት የተፈፀመውን አሳዛኝ ድርጊት መነሻ በማድረግ በመተከል ዞን ከሚመራው ኮማንድ ፖስት አመራር አካላት ጋር በዞኑ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ መክረዋል፡፡

ህይወታቸውን ላጡ ዜጎች ቤተሰቦች እና ወዳጆችም መፅናናትን ተመኝተዋል፡፡

በዞን የተለየዩ አካባቢዎች ያለውን የፀጥታ ችግር ለመፍታት ኮማንድ ፖስት ተደራጅቶ የራሱን ዕቅድ አዘጋጅቶ ከማህበረሰቡ ጋር በመቀናጀት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ቢሆንም፤ አሁንም የዜጎች ህይወት በአሳዛኝ ሁኔታ መጥፋት መቀጠሉ በውይይቱ ወቅት በቀረበ ሪፖርት ተጠቅሷል፡፡

በዚህ አካባቢም ሆነ በሌሎች ሠላምና ፀጥታን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመፍጠር የሴረኞችን ገመድ መበጣጠስ፣ ጠንካራ የህግ የበላይነትን ማስከበር ህብረተሰቡ ራሱን የመከላከል አቅም እንዲኖረው ማድረግ ወሳኝ ተግባር መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመተከል ዞን በተደጋጋሚ በሚከሰተው የፀጥታ ችግር የዜጎች ህይወት መጥፋት አሳዛኝ እና ልብ ሰባሪ ክስተት መሆኑን በመግለፅ ድርጊቱን በፅኑ ኮንነዋል፡፡

በቀጣይ ወንጀለኞችን እና ሃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አካላትን በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታልም ብለዋል።

የኮማንድ ፖስት አመራሩ የተያዘውን ዕቅድ በሁሉም አካባቢ በፍጥነት ተግባራዊ በማድረግ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ የበለጠ መተማመን ፈጥሮ መደበኛ ህይወት እንዲቀጥል ማሳሰባቸውን ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡