የሀገር ውስጥ ዜና

የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ

By Tibebu Kebede

October 15, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈፃፀም ግምገማ ተካሄደ።

በመድረኩም የመስኖ ልማት ኮሚሽን በባለቤትነት የሚያስገነባቸው የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የ2013 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የጥናት፣ የዝርዝር ዲዛይንና ክለሳ፣ የግንባታ ፕሮጀክቶች እና የወጣቶች መስኖ ልማት ፕሮጀክት አፈፃፀም ተመልክቷል።

በግምገማው ላይ በውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ መሪነት የዘርፉ ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት በትናንትናው እለት ተካሂዷል።

በግምገማው ወቅት ጥናት፣ ዝርዝር ዲዛይንና ክለሳ 22 ፕሮጀክቶች ፣ 9 ነባር የግንባታ ፕሮጀክቶች ፣ በ2013 በጀት ዓመት የሚጀመሩ  14 አዲስ ፕሮጀክቶች እንዲሁም የወጣቶች መስኖ ልማት ፕሮጀክት ባለፉት ሶስት ወራት  ውስጥ ከታቀደው ዕቅድ አንፃር  ያሉበት ደረጃ አጠቃላይ ሪፖርት  ቀርቧል።

የውሃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር  ዶክተር ኢንጂነር በሩብ ዓመቱ ውስጥ ከፍተኛ ዝናብ የነበረበትና ለፕሮጀክቶች ግንባታ ስራ ከባድ መኪኖችና ማሽነሪዎችን ማንቀሳቀስ አስቸጋሪ መሆኑ ቢታወቅም በቀጣይ 9 ወራት ውስጥ ያለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ያልተከናወኑትን በማካካስ የሚሰራበትን ዕቅድ በማውጣት በጥብቅ ክትትል እንዲፈፀም አሳስበዋል።

ሚኒስቴር መስሪያቤቱም ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ማስታወቃቸውን ከውሃ፣ ከመስኖ ልማት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።