አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 6 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም እና የአደጋ መከላከል ሥራዎችን ለማዘመን የሚያስችሉ ሶስት የሰው አልባ በራሪ ቁሶችን (ድሮን) ከጀርመን መንግስት በድጋፍ አገኘ።
በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ስቴፈን ኡር ድሮኖችን ለግብርና ሚኒስትሩ ኡመር ሁሴን አስረክበዋል።
የአንዱ ድሮን ዋጋ 28 ሺህ ዩሮ ሲሆን በአንድ በረራ ያለማቆራረጥ ለ90 ደቂቃ ያህል የመብረር አቅም እንዳላቸው ተገልጿል፡፡
በአንድ ጊዜም 700 ሄክታር መሬት የሚሸፍን መሬት የምስል መረጃን በማንሳት መያዝ ይችላሉ ተብሏል።
ድሮኖቹ ከመሬት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በማሰባሰብ ውጤታማ ስራዎችን ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በተለይም በተደጋጋሚ ድርቅ እያጠቃቸው ለሚገኙት አፋርና ሶማሌ ክልሎች ወቅታዊ መረጃዎችን በመላክ መንግሰት የአደጋ መከላከል ስራውን እና ሌሎች መፍትሄዎችን እንዲሰጥ አቅም እንደሚፈጥርለት ኢቢሲ ዘግቧል፡፡
በድጋፍ መልክ የተሰጡት በራሪ ቁሶች የኢትዮጵያን የደህንነትና የሲቪል አቪየሽን መስፈርት ያሟሉ መሆናቸም ተመልክቷል ።