የሀገር ውስጥ ዜና

በደቡብ ክልል 143 ሺህ ሄክታር መሬት የበቆሎ ሰብል በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እየለማ ነው

By Meseret Awoke

October 19, 2020

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 9፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል 143 ሺህ ሄክታር መሬት የበቆሎ ሰብል በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እየለማ መሆኑ ተገለጸ፡፡

የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳ በቤንች ሸኮ ዞን በኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ እየለማ ያለን የበቆሎ ሰብል የጎበኙ ሲሆን በጉብኝቱ ላይ ወረዳው የኤክስፖርት ሰብሎች የሚመረቱበት አካባቢ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቡናና ቅመማ ቅመምን ጨምሮ ከፍተኛ የሩዝ የበቆሎና የቅባት እህሎች የሚመረቱበት አካባቢ በመሆኑ ለክልሉ ብሎም ለሀገሪቱ ህዝቦች በምርት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ፋይዳ ያለው ሲሆን የውጭ ምንዛሬ ለማግኘትም ሚናው የላቀ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለአርሶ አደሩ ዘመናዊ የግብርና ግብአት ቴክኖሎጂዎችን ከታክስ ነጻ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተከናወነ ነውም ብለዋል፡፡

የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍቅሬ አማን በጉብኝቱ ላይ አርሶ አደሮች የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ባከናወኑት የልማት ስራ ውጤታማ ስራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም በሄክታር 120 ኩንታል በቆሎ እየተመረተ መሆኑን ከደቡብ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡