አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኢትዮጵያ አብዛኛው አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ መከሰቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።
የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ የተከሰተው ከጣና በለስ ወደ ባህርዳር የሚሄድ 400 ኪሎ ቮልት የሚሸከም የኃይል መስመር ላይ ባጋጠመ የቴክኒክ ችግር ምክንያት ነው ተብሏል።
በመስመሩ ላይ የተከሰተው የቮልቴጅ መዋዠቅ በአጠቃላይ የሃገሪቱ የኃይል አቅርቦት ላይ ችግር መፍጠሩን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለኢቢሲ አስታውቀዋል።
በዚህም ምክንያት በዛሬው እለት ከረፋዱ 5 ሰአት ጀምሮ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ ተከስቷል ነው የተባለው።
ችግሩን በአፋጣኝ ለመቅረፍ በተሰሩ ስራዎች አንዳንድ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት መጀመራቸውን እና ችግሩን ሙሉ ለሙሉ ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።