አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 16፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የከተሞች ሳምንት ምክንያት በማድረግ “የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮጀክት ለከተሞች ብልጽግና” በሚል መሪ ሐሳብ በደሴ ከተማ በመካሄድ ላይ ነው።
በመርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ተመስገን ጥሩነህን ጨምሮ የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጅነር አይሻ መሐመድ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ ሚኒስትሮችና ሌሎች የክልልና የፌደራል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች እየተሳተፉ ነው።
እንደ ሀገር የመጀመሪያው ዙር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ጥቅል አፈጻጸም ቀርቦ ውይይት ይደረግበታል ተብሏል።
የተመዘገቡ ውጤታማ ተግባራትን በማስቀጠልና ክፍተት የታየባቸውን አፈጻጸሞች በማረም በሁለተኛው ዙር የከተሞች ልማታዊ ሴፍቲኔትና የወጣቶች የስራ ዕድል ፕሮጀክትን ለማስጀመር መወሰድ ስለሚገባቸው እርምጃዎችም ምክክር ይደረጋል።
በደሴ ከተማ ባለፉት ዓመታት በልማታዊ ሴፍቲኔት ታቅፈው ወደ ሥራ በመግባት የተሻለ ተግባር እያከናወኑ የሚገኙ ማህበራትም ይጎበኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሀገር ደረጃ በሁለተኛው ዙር የከተሞች ሴፍቲኔትና የወጣቶች የሥራ እድል ፕሮጀክት 83 ከተሞች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብመድ ዘግቧል።