አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) 1495ኛው የነብዩ መሃመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በዛሬው እለት በመላ ሀገሪቱ ተከብሯል።
1495ኛው የነብዩ መሃመድ የልደት በዓል (መውሊድ) በዓል በተለይም በአዲስ አበባ በታላቁ አንዋር መስጊድ ተከብሯል።
በአንዋር መስጊድ እየተካሄደ ባለው የበዓሉ አከባበር ላይም የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እድሪስና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎችን ጥሪ የተደረገላቸው የስራ ኃላሂዎች እና የምንቱ ተከታዮች ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ የተገኙት ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፥ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመልእክታቸው አክለውም፥ የአዲስ አበባ ከተማ የኃይማኖት መቻቻል፣ የአብሮነት እና የአንድነት ከተማ እንድትሆን ህዝበ ሙስሊሙ ላደረገው ተግባር ምስጋና አቅርበዋል።
በኃይማኖት ስም ሊከሰቱ የሚችሉ የግጭት አጀንዳዎችን በማክሸፍ፣ በማውገዝና ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ህዝበ ሙስሊሙና የእምነቱ መሪዎች ከፍተኛ አስተዋጽዖ ማድረጋቸውንም ገልፀዋል።
ባለፈው ክረምት ህዝበ ሙስሊሙ በኮሮና ቫይረስ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በገንዘብና በተለያዩ መልኩ ባደረገው ድጋፍ የብዙዎችን ህይወት መታደግ መቻሉን በመግለፅ፤ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባስተላለፉት መልዕክት በራሳችን ሀብት ለመጠቀምና ሉዓላዊነታችንን ለማስጠበቅ ከምንጊዜውም በላይ በጋራ ልንቆም የሚገባበት ጊዜ ነው ብለዋል።
“ዛሬም የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ለመዳፈር የሚሞክሩ በገዛ ሀብታችንና ንብረታችን የሚፎክሩ አንዳንድ ማስተዋል የሌላቸው መሪዎችን መስማት ጀምረናል” ብለዋል።
በራሳችን ሀብት ለመጠቀምና ሉዐላዊነታችንን ለማስጠበቅ ኢትዮጵያውያን ምንጊዜም የማይዘናጉበትና ወደ ኋላ የማይሉበት መሆኑን አንስተው፤ ዛሬም ከምንጊዜውም በላይ በጋራ ልንቆም የሚገባበት ወቅት ላይ ነው ያለነው በማለት አመልከተዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሐጅ ዑመር እድሪስ ባስተላለፉት መልእክትም፥ የሰው ልጅ የደስታ ቀኑን በተለያዩ መልኩ ያከብራል፤ እኛም ዛሬ ነብዩ መሃመድ የተወለዱበትን የደስታ ቀን ነው የምናከብረው ብለዋል።
ነብዩ መሃመድ በምድር ላይ ቆይታቸው በዓለም ዙሪያ በርካቶችን አግኝተዋል ያሉ ሲሆን፥ ረጅም ጊዜ ጦርነት ላይ የነበሩ አካላትም እንዲያቆሙ አድርገዋል ሲሉም ተናግረዋል።
ነብዩ መሃመድ አንድነትን እንድናጠናክር መክረዋል፣ ሰላምን የሰበኩ ነብይ ናቸው፣ እኩልነት እንዲረጋገጥ አድርገዋል ለዚህም ልንከተላቸው ይገባል ብለዋል።