አዲስ አበባ ፣ ህዳር 2 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የከተማዋ ነዋሪዎች በተለያዩ መንገዶች ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆናቸውን የሚገልጹበትን የተለያዩ መርሃግብሮች ለማስተባበር ዝግጅት ማጠናቀቁን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አንቺነሽ ተስፋዬ መርሃግብሮቹን በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሃላፊዋ የመከላከያ ሠራዊቱ የጽንፈኛው የህወሓት ቡድንን ወደ ህግ ለማምጣት እያደረገ ባለው ጥረት ህብረተሰቡ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆኑን የሚገልጽበትን የድጋፍ ጥያቄ የከተማ አስተዳደሩ መቀበሉን ተናግረዋል።
በዚህም ከነገ ጀምሮ በሚካሄደው የደም ልገሳ መርሃግብር ደማችን ለወገናችን እና ደማችን ለመከላከያ ሰራዊታችን በሚሉ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መሆናቸውን ለመግለጽ ሠላማዊ ሰልፍ የሚደረግ ሲሆን÷ በሰልፉም የፀጥታ ችግሮች እንዳይፈጠር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ከኦሮሚያ የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር በተገቢው መንገድ ለማከናወን ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም አመላክተዋል።
በተጨማሪም ህብረተሰቡ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት ጎን መሆኑን ለማሳየት እንዲሁም ከሰራዊቱ ጎን ለተሰለፉ ሚሊሻዎች በገንዘብ እና ቁሳቁስ እንዲሁም ሙያዊ ድጋፍ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት፡፡
የህወሓት የማፍያ ቡድን ስልጣን የለቀቀው በዴሞክራሲያዊ ትግል ተሸንፎ ነው ያሉት ኃላፊዋ÷ ህብረተሰቡ እያሳየ ያለውን የአንድነት እና የሰላም እሴቶችን በማጠናከር ሀገሪቱን ወደ ተሟላ ህገመንግስታዊ ዴሞክራሲ ለማሸጋገር መረባረብ ይኖርበታልም ብለዋል፡፡
ሰላማዊ ሰልፈኞቹም ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመተባበር ሰልፎች በሰላም እንዲጠናቀቁ የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱና ራሳቸውንም ከኮቪድ 19 ስርጭት ለመከላከል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሬስ ሰክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።