አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) መንግስት ፅንፈኛውን የህወሓት ጁንታ ለህግ ለማቅረብ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊደግፈው እንደሚገባ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ፥ የህወሓት ጁንታ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱን ተከትሎ የኢፌዴሪ መንግስት ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለው ህግን ማስከበር ዘመቻ መቀጠሉን አስታውቋል።
የህወሓት ጁንታ ነባር አባል እና ቃል አቀባይ ይ ወጡ ቡድን የሰሜን እዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ማድረሱን በትናትናው እለት ማረጋገጣቸውን ያስታወሰው መግለጫው፥ መንግስትም ይህን ህገ ወጥ ቡድን ለህግ ለማቅረብ ያለው አቋም ከመቼውም ጊዜ በላይ ጠንካራ መሆኑን ገልጿል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በርካታ የክልሉን አካባቢዎች መቆጣጠሩን እና ነፃ ማውጣቱን ተከትሎም፤ ህገ ወጡ ጁንታ የፈፀማቸው ወንጀሎች በይፋ መውጣት መጀመራቸውንም ጽህፈት ቤቱ ገልጿል።
የህገ ወጡ ህወሓት ቡድን ሚልሻዎች በማይካድራ በንጹሀን ዜጎች ላይ የፈፀሙትን ጭፍጨፋም ቡድኑ ዓለም አቀፍ ህጎችን እና ድንጋጌዎችን የጣሰ ተግባር መፈፀሙን ያመላክታልም ብሏል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የህውሃት ቡድን በንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ተግባር እንዲሁ ሊያልፉት እንደማይገባ እና በተቻላቸው አቅም ሁሉ ሊያወግዙት እንደሚገባም አሳስቧል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የፌደራሉ መንግስት በህገ ወጡ የህወሓት ጁንታ ወንጀለኞችን ለህግ ለማቅረብ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ሊደግፉት እንደሚገባም የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ የሚያደርጉ ቡድኖችን እና ግለሰቦችን ለህግ ለማቅረብ እየተካሄደ ያለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ሲቪሎች እንዳይጎዱ የጥንቃቄ መስፈርቶችን በተከተለ መልኩ የሚካሄድ መሆኑንም ያረጋገጠው ጽህፈት ቤቱ፥ ዘመቻው ሲጠናቀቅ ውጤቱ በይፋ የሚታይ መሆኑንም ገልጿል።
ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አክሎም፥ ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉአላዊት ሀገር ህግን ለማስከበር የምታካሂደው ዘመቻ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የማካሄድ አቅም ያላት መሆኑንም አስታውቋል።
የሀገር ኩራት የሆነው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊትም ከራሱ ሀገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው ሀገራትም ስራውን በእውቀት የሚሰራ መሆኑን ያስመሰከረ ነው ብሏል መግለጫው።
የፌደራል መንግስት የህገ መንግስቱ በተሰጠው ስልጣን መሰረት ህግን የማስከበር ስራውን የሚቀጥል መሆኑንም ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አስታውቋል።
በዶክተር ሙሉ ነጋ ዋና ስራ አስፈፃሚነት የሚመራው እና በትግራይ ክልል የተቋቋመው ጊዜያዊ አስተዳደር በክልሉ የህግ የበላይነት እንዲከበር እና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እንደሚያደርግ እምነቱ መሆኑንም አስታውቋል።