የሀገር ውስጥ ዜና

በትግራይ ክልል እየተወሰደ ያለው ህግ የማስከበር እርምጃ ህገ መንግስታዊ ስርአትን ማስጠበቅ ነው – አምባሳደር ነብያት ጌታቸው

By Tibebu Kebede

November 17, 2020

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 8 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግስት በትግራይ ክልል የጀመረው ሕግ የማስከበር እርምጃ ዓላማው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የናደውን የመቐለ ጁንታ ለሕግ ተገዥ የማድረግና ሕገ መንግስታዊ ስርዓትን ማስጠበቅ መሆኑን በአልጀሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ገለጹ።

አምባሳደር ነብያት ከአልጄሪያው ዕለታዊ የዓረብኛ ጋዜጣ አል ፋጅር ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም በኢትዮጵያ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ስራዎችና የተገኙ ውጤቶችን፣ እየተካሄደ ያለውን የፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ስራዎችን አንስተዋል።

በዚህም ለዴሞክራሲ ማበብ የሕግ የበላይነት መከበር ወሳኝ መሆኑን፣ ማንኛውም ሀገር ህግን የተላለፉ አካላት በሚኖሩ ጊዜ ህግን የማስከበር ስራ እንደሚሰራ ሁሉ የኢትዮጵያ መንግስትም በትግራይ ክልል ህግ የማስከበር ዘመቻ እያካሄደ መሆኑን አስረድተዋል።

በሌላ በኩል የኢትዮጵያንና የአልጀሪያን ግንኙነት በፖለቲካ፣ በንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለማጠናከር በአልጀሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሚሲዮን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በአልጄሪያ በኩልም ግንኙነቱን በሚያጠናክሩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ተባብሮ ለመሥራት ሙሉ ዝግጁነት እንዳለ አስታውቀዋል።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያም የኢትዮጵያን አቋም ማስረዳት መቻሉንና ለአልጄሪያ የተለያዩ አካላትም ወቅታዊ መረጃ እንዲደርሳቸው መደረጉን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አል- ፈጅር ሚድያ በአልጀሪያ፣ በመካከለኛው ምስራቅና ሰሜን አፍሪካ ሠፊ ተከታዮች ያለው ሚዲያ ነው።