የሀገር ውስጥ ዜና

በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከተ ጉብኝት ተካሄደ

By Tibebu Kebede

December 07, 2020

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 28 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እንድሪስ የተመራ የልዑክ ቡድን በጄዳ የሥራ ጉብኝት አድርጓል።

ጉብኝቱ በሳዑዲ አረቢያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ጉዳይ በቅርበት ለማየትና የማህበረሰቡን ችግሮች ትኩረት ሰጥቶ በመመልከት ያለበትን ችግር በተቀናጀ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት የተደረገ ነው ተብሏል።

እንዲሁም የዳያሳፖራውን የልማት ተሳትፎና የሀብት ፍሰት ለማሳደግ በማሰብ መሆኑም ተጠቁሟል።

በውጭ የሚኖረው ማህበረሰብ ተወካይ እንዲኖረው በፖሊሲ መልክ የህግ ማዕቀፍና ተቋማዊ ይዘት ዝግጅት ተደርጎ የዳያስፖራ ኤጀንሲ ወደ ስራ መግባቱ ነው የተነገው።

በጄዳና አካባቢው ያለውን ማህበረሰብ የልማት ተሳትፎ ከማሳደግ፣ የኮሚኒኬሽን መረጃና ጥናትን ከማጠናከር ብሎም የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅና የህግ ከለላውን ለማጠናከር በሚያስችሉ ሥራዎች ዙርያ ጄዳ ከሚገኘው የኢ.ፊ.ዲ.ሪ ቆንስላ ጽህፈት ቤትና በጄዳና አካባቢው ከሚኖረው ማህበረሰብ ተወካዮች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል መባሉን ከፅህፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የልዑካን ቡድኑ በቀጣይ ቀናት በጄዳና ሪያድ ከሚገኙ የተለያዩ አካላትና ከሳዑዲ መንግስት ተወካዮች ጋር በእነዚሁ ጉዳዮች ላይ የሀሳብና የመረጃ ልውውጥ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።