አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 6፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ክልል በቱሪዝም ዘርፍ በቀጣይ 5 ዓመታት ውስጥ ለ500 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር መታቀዱን የክልሉ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታወቀ።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ሌሊሴ ዱጋ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፥ ኦሮሚያ ክልልን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግስት የቱሪዝም ሀብት ለሀገር ያለውን አስተዋጽኦ እና የሥራ እድል ለመፍጠር ያለውን ሚና በመገንዘብ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም ኮሚሽነሯ ጠቁመዋል።
አያይዘውም በቱሪዝም ዘርፍ በቀጣይ 5 ዓመታት በክልሉ ለ500 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠርና በክልሉ በሚገኙ የመስህብ ስፍራዎችን የሚኖሩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የኦሮሚያ ክልልን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ኮሚሽኑ የኦሮሚያ ክልል የቱሪዝም ሐብት ማጥናት፣ መመዝገብና ማስተባበር ላይ እንደሚገኝም አውስተዋል።
ኮሚሽኑ የመስህብ ስፍራዎችን በዘመናዊና በተቀላጠፈ መንገድ ለማስተዋወቅና ለማልማት አቅዶ የተመሠረተ ተቋም መሆኑን አክለዋል።
ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ቀን ጀምሮ ላለፉት 5 ወራት የሰራቸውን ሥራዎችና ወደፊት ሊሰራቸው ያቀዳቸውን ሥራዎች በተመለከተ ማብራሪያ መስጠታቸውን የኦሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መረጃ ያመለክታል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመስህብ ስፍራነት ተለይቶ እየተሰራበት ያለው የወንጪ ሐይቅን ጨምሮ ሌሎች የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ሀብቶችን ለማልማትም እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል።