የሀገር ውስጥ ዜና

የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል በሠላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የፀጥታ አካላት አስታወቁ

By Abrham Fekede

December 23, 2020

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14፣ 2013(ኤፍቢሲ) ዓመታዊው የቁልቢ ገብርኤል የንግስ በዓል በሠላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን የምስራቅ ኢትዮጵያ የፀጥታ አካላት አስታወቁ፡፡

የሀረሪ ክልል፣ የድሬዳዋ አስተዳደር፣ የምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች የፖሊስ ኮሚሽኖችና የአስተዳደርና የፀጥታ የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም የፌደራል ፖሊስና የሃገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ.ም በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ሜታ ወረዳ በቁልቢ ከተማ የሚከበረው የቁልቢ ገብርኤል ዓመታዊ የንግስ በዓል ያለምንም የፀጥታ ችግር በሠላም ተከብሮ እንዲጠናቀቅ የሚያስችል ውይይት አድርገዋል፡፡

የፀጥታ አካላቱ በዓሉን ለማክበር ከሃገር ውስጥና ከውጭ ሃገራት የሚመጡ የእምነቱ ተከታዮችና ጎብኚዎች በዓሉን በሠላም አክብረው ወደ መጡበት እንዲመለሱ በጋራ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

ምዕመናኑ ወደ ንግስ በዓሉ ሲመጡ የሰዎች መጨናነቅ በሚበዛባቸው በደብሩ መግቢያና መውጫ በሮች፣ በክርስትና ቤትና በስለት ማስገቢያ እንዲሁም በቤተ መቅደሱ በሮችና በአጠቃላይ በዓሉ በሚከበርበት አካባቢ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ መጠቀምና አካላዊ ርቀትን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በዓሉ የሚከበርበት አካባቢም የመሬቱ አቀማመጥ ዳገታማ፣ ቁልቁለትና ጠመዝማዛ መንገዶች የሚበዙበትና የንግስ በዓሉን ለማክበር በርካታ ተሸከርካሪዎች ወደ ስፍራው የሚመጡ በመሆኑ አሽከርካሪዎች በከፍተኛ ጥንቃቄ ማሽከርከር እንደሚኖርባቸውና ከታህሳስ 18 ቀን 2013 እስከ ታህሳስ 19 ቀን ከሰዓት በኋላ ድረስ ከጨለንቆ ከተማ እስከ ቀርሳ ባለው ዋና መንገድ ላይ ከባድ ተሸከርካሪዎች ማለፍ እንደማይችሉና ሌሎች ተሸከርካሪዎችንም አቁሞ መሄድ የተከለከለ መሆኑ በውይይቱ ወቅት ተጠቅሷል፡፡

በዓሉን ለማክበር የሚመጡ ምዕመናንና ጎብኚዎችም የኮሮና ቫይረስን ከመከላከል ጎን ለጎን የግል ንብረቶቻቸውን፣ ጌጣጌጥና ገንዘብ በጥንቃቄ ሊይዙ እንደሚገባ ጥሪ ተላልፏል፡፡

የወንጀል ድርጊትቶች ተፈፅመው ሲገኙም አፋጣኝ ውሳኔ ለመስጠት በአካባቢው ጊዜያዊ ፍርድ ቤት እንደሚቋቋምና ፈጣን ውሳኔ እንዲሰጥ እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡

ፀረ ሠላም ኃይሎች በንግስ በዓሉ ወቅት ችግር እንዳያደርሱ የፀጥታ አካላት ከሚያደርጉት የተጠናከረ ጥበቃ ጎን ለጎን ህብረተሰቡ የአካባቢውን ደህንነት በንቃት እንዲጠብቅና አጠራጣሪ እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት በአቅራቢያው ለሚገኙ ፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥም ጥሪ ቀርቧል፡፡

የቁልቢ ገብርኤል ሃይማኖታዊ የንግስ በዓል በዓመት ሁለት ጊዜ ታህሳስ 19 እና ሐምሌ 19 ቀን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የእምነቱ ተከታዮችና ጎብኚዎች የሚታደሙበት ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል ነው፡፡

በተሾመ ኃይሉ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!