የሀገር ውስጥ ዜና

የፌደራል የዴሞክራሲ ተቋማት የጋራ የምክክር መድረክ በጅግጅጋ እየተካሄደ ነው

By Tibebu Kebede

December 25, 2020

አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 16 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ)የፌደራል የዴሞክራሲ ተቋማት የጋራ የምክክር መድረክ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ምክትል አፈ ጉባኤ ሽታዬ ምናለ፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መአዛ አሸናፊ እንዲሁም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አመራሮችና ለህዝብ ተወካዮች ተጠሪ የሆኑ የዴሞክራሲ ተቋማት እየተሳተፉ ነው፡፡

አቶ ታገሰ ጫፎ የምክክር መድረኩ እስካሁን የተከናወኑ ስራዎችና በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ በመምከር ለቀጣይ ስራ ጥሩ መሰረት የሚጣልበት መሆኑን ተናግረዋል።

የሶማሌ ክልል ለውጡን ተከትሎ ቀደም ሲል በክልሉ የነበሩ ተግዳሮቶችን በመፍታት የተሻለ የሰላምና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ማረጋገጥ መቻሉን የጠቆሙት አፈ ጉባኤው ምክር ቤቱ ለክልሉ የሚያስፈልገውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።

የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኢብራሂም ዑስማን በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ አስተማማኝ መሰረት ያለው የዴሞክራሲ ስርአት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የዴሞክራሲ ተቋማት ሚና እንዲያድግ ተቋማቱ ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ተኩረት ሰጥቶ መረባረብ ይገባል ብለዋል።

በሀገሪቱ የዴሞክራሲ ተቋማት ያለባቸውን ሀላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ ለማስቻል ተቋማዊ አደረጃጀታቸውንና ነፃነታቸውን በማጠናከር በአሰራር፣ በሰው ሀይልና በቴክኖሎጂ መገንባት እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

የምክክር መድረኩ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የ5 አመት ረቂቅ ስትራቴጂ፣ የምርጫ ቦርድ ሪፎርምና በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን የሪፎርም ስራዎች ላይ ያተኮሩ ፅሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው የሶማሌ ክልል ቴሌቪዥን ዘግቧል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!