አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 20 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛ ዓመት 5ኛ የሥራ ዘመን 6ኛ አስቸኳይ ጉባዔ የአራት የምክር ቤት አባላትን ያለመከሰስ መብት አንስቷል፡፡
ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው
1. አቶ አድጎ አምሳያ
2. አቶ ሽፈራው ጨሊቦ
3. አቶ ግርማ መኒ እና
4. አቶ አረጋ ባልቢድ ናቸው፡፡
ምክር ቤቱ በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ያለመከሰስ መብታቸው እንዲነሳ የቀረቡትን የምክር ቤት አባላት ያለመከሰስ መብት በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በመተከል ዞን በንጹኃን ዜጎች ላይ የተፈጠረው ችግር የከፋ ያደረገው አመራር የተሳተፈበት መሆኑን ጠቅሰው ዞኑን ከማረጋጋት አልፎ ዘላቂ መፍትሄ እንዲያገኝ በድርጊቱ በተሳተፉ አካላት ላይ የተጀመረው የህግ የበላይነትን የማስከበር ዘመቻ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡
በክልሉ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ያኮረፉ አካላት፣ ህዝቦች እንዳይረጋጉና በሠላም እንዳይኖሩ እያደረጉ በመሆኑ ከመንግስት ቁርጠኛ እርምጃ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
እናቶች፣ ህጻናትን ጨምሮ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ለተፈናቀሉ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈም አካባቢውን አረጋግቶ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ መሥራት ይገባልም ብለዋል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታደለ ተረፈ በመተከል ዞን በዜጎች ላይ የደረሰው ጥቃት እጅግ አሳዛኝና ሊደገም የማይገባው ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይ ተጨማሪ ሞት፣ መፈናቀልና ጉዳት እንዳይከሰት የምክር ቤት አባላትን ጨምሮ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ማሳሰባቸውን ከክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!