አዲስ አበባ ፣ ታህሳስ 22 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የካዳስተር ስርዓት ለመሬት አስተዳደር ስርዓት መዘመን ሞተር በመሆን ዘላቂ ሀገራዊ ልማትን ለማምጣት አቅም እንደሚፈጥር የፌደራል ከተማ መሬት እና መሬት ነክ ንብረት ምዝገባ እና መረጃ ኤጄንሲ አስታወቀ፡፡
ኤጀንሲው ባለፉት ዓምስት ዓመታት በተካናወኑ ስራዎች እና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ የተለያዩ የክልል እና የፌደራል ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ውይይት እያካሄደ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ በህጋዊ ካዳስተር እና የመሬት ይዞታ ምዝገባ የዜጎችንና የመንግስትን የማይንቀሳቀስ ንብረት መብት የህግ ከለላ እንዲያገኝ በማድረግ በከተሞች የመልካም አስተዳደርን ውጤታማነት በላቀ ደረጃ መምራት እንደሚያስችልም ተመላክቷል፡፡
ኤጀንሲው በ2022 ዓ.ም ኢትዮጵያን “አፍሪካዊ የብልፅግና ተምሳሌት”ለማድረግ የተያዘውን ሀገራዊ ራዕይ ለማሳካት የራሱን እቅዶች በመቅረፅ እየተንቀሳቀሰ ነውም ተብሏል፡፡
ባለፉት አምስት ዓመታትም በ18 ከተሞች የ1 ነጥብ 4 ሚሊየን መሬቶች ይዞታ የመመዝገብ እና የማረጋጋጥ ስራ ለማከናወን ታቅዶ 435 ሺህ የሚሆነው ብቻ መከናወኑ በመድረኩ ተነስቷል፡፡
ለእቅዱ አነስተኛ መሆንም የባለድርሻ አካላት ክትትል እና ትኩረት አነስተኛ መሆን፣ ለሚሰሩ ስራዎች ወጥ እና የተደራጀ ሰነድ አለማዘጋጀት፣ የህግ ማዕቀፎች አለመኖር እና በዘርፉ በቂ እውቀት እና ልምድ ያለው ባለሙያ እጥረት ዋነኛ ችግሮች መሆናቸው ተጠቁሟል፡፡
በቀጣይ 5 ዓመታትም በ60 ከተሞች ከ3 ሚሊየን በላይ የከተማ መሬቶችን ይዞታ የመመዝገብ እና የማረጋጋጥ ስራ ለማከናወንማቀዱን ኤጄንሲው አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ዜጎች በካዳስተር ስርዓት ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተመላክቷል፡፡
በመላኩ ገድፍ
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!