አዲስ አበባ ፣ታህሳስ 28 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ባለፉት 6 ወራት ከ63 ቢሊየን ብር በላይ በሚገመቱ የመንግስት ተቋማት የፍትሐ ብሔር ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ ማድረጉን አስታወቀ።
ባለፉት ስድስት ወራት ከተለያዩ የመንግስት ተቋማት ጋር በቅንጅት በመስራት በድምሩ 63 ቢሊየን 741 ሚሊየን 12 ሺህ ብር በሚገመቱ የተቋማቱ የፍትሐ ብሔር ጉዳዮቸ ዙሪያ የተለያዩ የአገልግሎት ዓይነቶችን በመስጠት ተሳትፎ እንዳደረገ የፍትሐ ብሔር ፍትህ አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ገልጿል።
ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(4) ስር የተሰጡት ዝርዝር የፍትሐ ብሔር ሥልጣንና ኃላፊነቶች ተቋሙ የተጣለበትን የህዝብ እና የፌዴራል መንግስቱን የፍትሐ ብሔር ጥቅም የማስጠበቅ ዓላማ ለማሳካት የሚረዱ መሆናቸው ተጠቁሟል።
ለመንግስት ተቋማት በፍትሐ ብሔር ጉዳዮቻቸው ረገድ የሚያደርገው ድጋፍ የፍትሐ ብሔር የህግ ምክር በመስጠት፣ የግዙፍ ፕሮጀክቶች ውሎችን ጨምሮ በተለያዩ የውል ጉዳዮች ላይ ከተቋማቱ ጋር በጋራ በመሆን በመደራደር፣ የመንግስት ተቋማት የሚያጋጥሟቸው ፍትሐ ብሔራዊ አለመግባባቶች በአማራጭ የግጭት መፍቻ ዘዴዎች እንዲቋጩ በማድረግ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት ተቋማቱ በሚከስሱባቸው ወይም በሚከሰሱባቸው ጉዳዮች ላይ በተናጥል ወይም ከተቋማቱ ጋር በጋራ በመወከል እና ፍርዶችን በማስፈጸም ረገድ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የተደረገው ተሳትፎ ሁሉንም የፍትሐ ብሔር የአገልግሎት ዓይነቶች ያካተተ እንደሆነ የገለጸው ዳይሬክቶሬት ጄነራሉ ከተቋማቱ ጋር በጋራ ለመስራት የሚደረገው ጥረት ተቋማቱ በተቋቋሙለት ዓላማ ላይ ሙሉ ትኩረታቸውን እንዲያደርጉ እና ፍትሐ ብሔራዊ በሆኑ ጉዳዮች ምክንያት ውጤታማነታቸው እንዳይስተጓጎል ብሎም የህዝብና የመንግስት ሀብት እንዳይባከን የማድረግ ዓላማን ያነገበ ነው፡፡
በተጨማሪም በስድስት ወራቱ የአፈጻጸም ጊዜ ውስጥ ከ1 ሺህ 200 በላይ ለሚሆኑ የገንዘብ አቅም የሌላቸው ዜጎች የፍትሐ ብሔር ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎት መሰጠቱን ዳይሬክቶሬት ጄነራሉ አስታውቋል፡፡
በቀጣይ ቀሪ የእቅድ ጊዜያት ውስጥም ኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከተቋማቱ ጋር ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር አጠናክሮ በማስቀጠል የህዝብና የመንግስትን ፍትሐ ብሔራዊ ጥቅም በተሻለ ለማስጠበቅ ጥረት የሚደረግ መሆኑን ዳይሬክቶሬት ጄነራሉ ገልጾ ለዚህ ዓላማ መሳካት ሁሉም የመንግስት ተቋማት ፍትሐ ብሄራዊ የሆኑ ጉዳዮቻቸውን በማቅረብ በቅንጅት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!