የሀገር ውስጥ ዜና

የአጅማ ጫጫ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ

By Tibebu Kebede

January 09, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 1 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የአጅማ ጫጫ መስኖ ልማት ፕሮጀክት በይፋ ተጀመረ፡፡

ፕሮጀክቱ በዞኑ አንጎለላ ጠራ ወረዳ የሚገነባ ሲሆን፥ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር እና የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በይፋ አስጀምረውታል።

ግድቡ 45 ነጥብ 5 ሜትር ከፍታ እና 371 ሜትር ርዝመት ሲኖረው 55 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም ይኖረዋል።

በ5 ቢሊየን ብር በጀት የሚገነባው ፕሮጀክት ግንባታ በሶስት አመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም 7 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከ28 ሺህ በላይ አባወራዎችንና እማወራዎችን ተጠቃሚ ያደርጋልም ነው የተባለው።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር በክልሉ ከዚህ ቀደም የተጀመሩ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች በመዘግየታቸው ምክንያት አርሶ አደሩን ሲጎዱ እንደነበር ጠቅሰው ከሁለት አመት ወዲህ በተደረገ ለውጥ ግን አፈጻጸማቸው ተቀይሮ አሁን አርሶ አደሩን መጥቀም መጀመራቸውን ተናግረዋል።

የአጅማ ጫጫ መስኖ ፕሮጀክትም በተያዘለት ጊዜ፣ በጀትና ጥራት ልክ ተጠናቆ የአካባቢውን አርሶአደር እንደሚጠቅም እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ የካሳ ክፍያ ሳይከፈለው ገና በሂደት ላይ እያለ ቦታውን በመስጠት ፕሮጀክቱ እንዲጀመር በማድረጉ ምስጋና አቅርበዋል።

የውሃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው መንግስት የአርሶአደሩን ህይወት ለመቀየርና ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ የግብርናው ዘርፍ ላይ የሪፎርም ስራ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

ከዚህ ሪፎርም መካከል በመስኖ ልማት አርሶአደሩ በአመት እስከ ሶስት ጊዜ ድረስ እንዲያመርት የሚያስችል የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት በተያዘው ዓመት ለነባርና አዳዲስ ፕሮጀክቶች 16 ቢሊየን ብር በጀት መድቧልም ነው ያሉት።

በዘመን በየነ

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!