የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያና ስዊድንን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራ ተጠቆመ

By Tibebu Kebede

January 11, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 3 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያንና ስዊድንን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ነገሪ ሌንጮ ገለጹ ፡፡

ዶክተር ነገሪ በኢትዮጵያ የስዊድን አምባሳደር ሄኒክ ሉንዲክ ጋር ተወያይተዋል።

ሁለቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ ዲፕሎማሲያዊ ታሪክ እንዳላቸውና የሁለትዮሽ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር የፓርላማ የወዳጅነት ቡድን በመመስረት እና የሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር እንደሚሰራ በዚህ ወቅት ተናግረዋል።

ወዳጅነቱ ፍሬያማና ውጤታማ እንዲሆን ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ከስዊድን ጋር በጋራ እንደምትሰራም ነው የተናገሩት።

ስዊድን በሀገሪቱ በተለይም በትምሕርት ቤት ግንባታ በኩል ላደረገችው ድጋፍ አመስግነው በትግራይ ክልል የተከናወነውን የሕግ ማስከበር እርምጃ አስመልክተው አብራርተውላቸዋል፡፡

በአምባገነኑ የሕወሓት ቡድን ላይ የተወሰደው እርምጃ እንደተጠናቀቀና በክልሉ ሰላም መስፈን እንደቻለ አስረድተው፥ በሕግ ማስከበር እርምጃው ከቀያቸው ተፈናቅለው ለነበሩ የህብረተሰብ ክፍሎች መንግስት አስፈላጊውን የሰብዓዊ እርዳታ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

መንግስት ሕገ-ወጡ ቡድን ያፈራረሳቸውን መሰረተ ልማቶች ወደነበሩበት የመመለስ ስራ እየሰራ መሆኑን አውስተዋል።

የስዊድን ባለሃብቶች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ እንዲሰማሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

አምባሳደር ሉንዲክ በበኩላቸው ሀገራቸው በኢንቨስትመንት፣ በንግድና የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ከኢትዮጵያ ጋር ትሰራለች ብለዋል።

አምባሳደሩ አክለውም የሃገራቸው ባለሃቶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ እንዲሰማሩ ለማድረግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!