አዲስ አበባ ፣ ጥር 13 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሳንጃ የፍተሻ ኬላ በህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ውስጥ ቱርክ ሰራሽ የሆኑ 62 ሽጉጦች መያዙን ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ሽጉጦቹ የተያዙት ትናንት ረፋድ በታች አርማጭሆ ወረዳ በሳንጃ ከተማ የፍተሻ መቆጣጠሪያ ኬላ ላይ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የኮሙዩኒኬሽን እና ሚዲያ ዋና ክፍል ሃላፊ ኮማንደር ውብነህ አስናቀው ለኢዜአ ተናግረዋል።
የጦር መሳሪያው መነሻው በሱዳን ድንበር ከሚገኘው የአብርሃ ጅራ ከተማ ሆኖ ወደ ጎንደር ከተማ ለማስገባት የታቀደ እንደነበርም ኮማንደሩ ጠቁመዋል፡፡
ሽጉጦቹ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-08517 አማ በሆነው የህዝብ ማመላለሻ ሚኒባስ ውስጥ በስውር በተዘጋጀ የተሽከርካሪው አካል ውስጥ ተደብቆ በጉምሩክ ፈታሾች እና ፖሊሶች አማካኝነት እንደተገኘ ገልጸዋል፡፡
በዚህ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የተጠረጠረው አሽከርካሪ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተረገበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሚኒባሱ ረዳት አሽከርካሪ ለጊዜው ማምለጡንም ተናግረዋል።
የሱዳን አዋሳኝ በሆነው ምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ ከተሞች የህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ሲፈጸም መቆየቱንም አስታውሰዋል፡፡
ህብረተሰቡ የጦር መሳሪያ አዘዋዋሪዎችን ተከታትሎ ለፖሊስ በመጠቆም በኩል እያደረገ ያለውን መልካም ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮማንደር ውብነህ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!