የሀገር ውስጥ ዜና

በህገወጥ የቤትና የመሬት ወረራ የተሳተፉ አመራሮችን ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ

By Abrham Fekede

January 29, 2021

በህገወጥ የቤትና የመሬት ወረራ የተሳተፉ አመራሮችን ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የመሬት ወረራ ሲፈፀም ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ላይ ከፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰዱን እና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ለሚመለከተው አካል ማስተላለፉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።

በአዲስ አበባ ከተማ በተፈፀመ የመሬት ወረራ እና ግንባታ ፣ በህገ ወጥ መንገድ በተያዙ የጋራ መኖሪያ ቤቶችና የቀበሌ ቤቶች ዙሪያ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ አቶ ጃንጥራር አባይ በዛሬው ዕለት ዝርዝር ማብራሪያ ተሰጥቷል።

አቶ ጃንጥራር አባይ በዝርዝር ማብራሪያቸው እንዳመላከቱት የከተማ አስተዳደሩ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ባሉት ጊዜያት እየሰፋ የመጣውን የመሬት ወረራው እና ህገወጥ ግንባታን ለማስቆም እና በዘርፉ የሚስተዋለውን ስርዓት አልበኝነት ከምንጩ ለማድረቅ ጥናት ማካሄዱን ገልጸዋል ።

ማንም ግለሰብም ይሁን ቡድን የሚሰጠው ጥቆማ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ገልፀው አዲሱ አመራር ከመጣበት ግዜ ጀምሮ ድርጊቱን ለመከላከልም ሆነ ባለበት ለማቆም ጥናት ማካሄድ እንዳለበት አምኖበት ያስኬደው መሆኑን ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የጥናቱን ግኝቶች እና መረጃዎች አባሪ አድርጎ ደብዳቤ መላኩንም አስታውቋል።

በማብራሪያቸው ጥናቱ በከተማ አስተዳደሩ ሁሉም ክፍለ ከተሞች መካሄዱን አብራርተዋል።

ጥናቱን ለማካሄድ በተቋቋመው ኮሚቴም በየ15 ቀኑ ግምገማ ያደርግ እንደነበር ነው ያነሱት።

ከ21 ሺህ በላይ በህገወጥ መንገድ የተለዩ የጋራ መኖርያ ቤቶች፣ 322 ባለቤት አልባ ቤቶችና ከ1 ሺህ 338 ሄክታር በላይ መሬት በጥናቱ መለየቱን ይህም ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ሲሰራ የነበረ መሆኑን በጥናቱ ተለይቷል ብለዋል።

በከተማዋ የመሬት ወረራ ሲፈፀም ሃላፊነታቸውን ባልተወጡ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ላይ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ተወስዷል፣ በቀጣይም እርምጃው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ጃንጥራር ተናግረዋል ።

በዚህ ህገወጥ ስራ ላይ በተሰማሩት ላይ አስተዳደራዊና ፖለቲካዊ እርምጃ ወስደናል ያሉት አቶ ጃንጥራር ህጋዊ በሆነ መልኩ በዚህ ስራ ላይ የተሳተፉትን ተጠያቂ ለማድረግ የከተማ አስተዳደሩ ለፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ያገኛቸውን መረጃዎች አባሪ አድርጎ ደብዳቤ መላኩን ገልፀዋል፡፡

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!