የሀገር ውስጥ ዜና

የሀረሪ ክልል ለሲዳማ ክልል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

By Meseret Awoke

January 30, 2021

አዲስ አበባ፣ ጥር 21፣ 2013(ኤፍ ቢ ሲ) የሀረሪ ክልል ለሲዳማ ክልል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ።

የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በዛሬው እለት የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ የልኡካን ቡድን አባላትን በጽ/ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

የሲዳማ ክልል ልኡካን ቡድን በሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ ጉዞ እንደሚያደርግና የመጀመሪያ መዳረሻውን ሀረሪ ክልል ማድረጉን አሳውቋል።

ከአገራችን ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታ በመነሳት የፌዴራሊዝም ሥርዓቱ እስከአሁን የነበሩበትን ችግሮችና ክፍተቶች በማረም ወደሚፈለገው እውነተኛ ፌዴራሊዝም ከማሸጋገር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ ያሰመሩበት የቡድኑ አባላት ለዚህም በክልሎች መካከል የመደጋገፍና አብሮ የመስራት ባህል መፈጠርና መጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል።

ስለሆነም የሲዳማ ክልላዊ መንግስት አዲስ የተቋቋመ እንደመሆኑ መጠን እስከሚጠናከር ድረስ ከሌሎች እህት ክልሎች ሁለንተናዊ ድጋፎችን እንደሚጠብቅ በመጠቆም የሀረሪ ክልልም የበኩሉን እገዛ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

የሲዳማ እንደ ክልል መመስረቱ አዲስ ቢሆንም ከጅምሩ አንስቶ በሁሉም ዘርፎች አጥጋቢ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ መገንዘባቸውን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ “የጉዟችሁ ቀዳሚ መዳራሻ ስላደረጋችሁን እኛም አቅም በፈቀደ መጠን ተገቢውን ድጋፍ በማድረግ የመጀመሪያዎቹ እንሆናለን” ብለዋል።

አያይዘውም ከክልሉ ጋር በሁለንተናዊ መስኮች ከመደጋገፍ ባለፈ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና ሌሎች የህበረተሰብ ክፍሎች ከአቻዎቸው ጋር እንዲተዋወቁ፣ እንዲቀራረቡና ተደጋግፈው ለጋራ ብልጽግና እንዲሰሩ ለማስተሳሰር፣ ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙት ለመፍጠር ቁርጠኛ ፍላጎት እንዳላቸውም ገልጸዋል።

የካቲት 15 ቀን 2013 ዓ.ም በሀዋሳ ከተማ በሚካሄደው የሲዳማ ክልል ምስረታና ገቢ ማሰባሰቢያ በዓል ላይ የሀረሪ ክልል እንዲሳተፍ ግብዣ ቀርቦለታል።

አቶ ኦርዲንም በሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደሚገኙ ለልኡካን ቡድኑ አባላት አረጋግጠውላቸዋል።

የሲዳማ ክልል የካቲት 15 የሁሉም ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችና የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች የሚሳተፉበት ፕሮግራም ማዘጋጀቱ ተገልጿል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!