አዲስ አበባ ፣ ጥር 24 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለክቡር ዶ/ር አርቲስት ዓሊ ቢራ የምስጋና እና እውቅና ፕሮግራም ማዘጋጀቱን ገለፀ፡፡
የኦሮሚያ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ከበደ ዴሲሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳታወቁት የእውቅናና የምስጋና ፕሮግራሙ ጥር 30 ቀን 2013 ዓ.ም በተለያዩ ዝግጅቶች ይካሄዳል፡፡
እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለፃ ክቡር ዶ/ር አርቲስት ዓሊ ቢራ ከ60 ዓመታት በላይ ለኦሮሞ ህዝብ ጥበብ ፣ ባሕል እና ቋንቋ እድገት ጉልህ ሚና ያበረከተ ታላቅ ሊቅ ነው፡፡
የምስጋናና የእውቅና ፕሮግራሙ አርቲስቱ ለህዝቦች ሁለንተናዊ እኩልነት እና አብሮነት ላበረከተው ከፍተኛ አስተዋፅዖ እውቅና ለመስጠጥ ታስቦ የተዘጋጀ ነው ብለዋል፡፡
ክቡር ዶ/ር አርቲስት ዓሊ ቢራ ጊዜያት ቢፈራረቁና ሁናቴዎች ቢቀያየሩም ለዓላማው በመፅናት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አበርክቷል ነው ያሉት፡፡
አርቲስት አሊ ቢራ በአፋን ኦሮሞ፣ አማርኛ፣ አፍ ሶማሊ፣ አፋርኛ፣ ሐረሪ ፣ አረብኛ እና በሌሎች ቋንቋዎችም ሙዚቃን ሲጫወት ኖሯል፡፡
አርቲስቱ በተስረቅራቂ ድምፁ ዘመን ተሸጋሪ ጥዑም ሙዚቃን ከመጫወት በተጨማሪ የግጥምና ዜማ ደራሲም ነው፡፡
ለጥር 30 በተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ የፌዴራል እና የክልል መንግሥት የስራ ኃላፊዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የጥበቡ ማኅበረሰብ፣ ቤተሰቦች፣ ጓደኞቹ እና አድናቂዎቹ በተገኙበት በዶ/ር ሱራፌል ገልገሎ የተዘጋጀው የአርቲስቱ የሕይወት ታሪክ እና ሥራዎች ላይ የተፃፈ መጽሐፍ የሚመረቅ ይሆናል፡፡
ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤
ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ
ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ
ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!