የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ክልል በቀጣይ አሥር ዓመታት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ እቅድ ተዘጋጅቷል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

By Tibebu Kebede

February 03, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 26 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በቀጣይ ዐሥር ዓመታት ውስጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ እቅድ መዘጋጀቱን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

በክልሉ የዐሥር ዓመት መሪ የልማት እቅድ ላይ የክልሉ አመራሮች እና ባለሞያዎች በጋምቤላ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል።

ርእሰ መስተዳድሩ በክልሉ ከ2003 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም ድረስ በሁለት የእቅድ እና ትራንስፎርሜሽን ዘመናት በርካታ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በመጀመሪያው እና ሁለተኛው የዕድገት እና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን በኢኮኖሚ እድገት፣ በመሠረተ ልማት፣ በማኅበራዊ ልማት እና በአቅም ግንባታ ዙሪያ ቀጣይነት ያላቸው ስኬታማ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታት በክልሉ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት በማስመዝገብ፣ የሥራ እድል በመፍጠር እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ርብርብ የተደረገ ቢሆንም፣ ሰፊ የሥራ እድል ከመፍጠር አንጻር ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም በቀጣይ አስር ዓመታት ውስጥ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል በማሳተፍ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ያለመ እቅድ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

ባለፉት ሁለት የእድገት እና ትራንስፎርሜሽን ዓመታት የተመዘገቡ መልካም ተሞክሮዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በቀጣይ አሥር ዓመታት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የክልሉ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ሓላፊ አቶ ኡቦንግ ኡቶው በበኩላቸው፣ በክልሉ ባለፉት የእቅድ ትግበራ ዓመታት የተገኙ ጥንካሬዎች እና መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት በቀጣይ አሥር ዓመታት በትኩረት መሥራት ይገባል ብለዋል።

በመድረኩ የክልል፣ የዞን እና የወረዳ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የፋይናንስ ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያዎች መሳተፋቸውን ከጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!