የሀገር ውስጥ ዜና

በቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ 61 የግል ድርጅቶችን ያቀፈ የትብብር መድረክ ተመሰረተ

By Meseret Demissu

February 04, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2013 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ የተሰማሩ 61 የግል ድርጅቶችን ያቀፈ የግል ዘርፍ የትብብር መድረክ ተመስርቷል፡፡

ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በመሆን የተመሰረተው የትብብር መድረኩ የግል ድርጅቶቹ በሀገሪቱ የዲጂታል ኢኮኖሚን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት አካል እንዲሆኑ ለማድረግ ነው፡፡

ድርጅቶቹ በኤሌክትሮኒክ ክፍያ፣ ኤሌክትሮኒክ ንግድ፣ በፋይናንሽያል ቴክኖሎጂ፣ በግብርና ቴክኖሎጂ፣ በትምህርት ቴክኖሎጂና በመደበኛ ንግድ ላይ የተሰማሩ ናቸው፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ÷ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ኃላፊነት የዘርፉን ማነቆዎች መፍታትና አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዲጂታል ኢኮኖሚ በመገንባት ረገድ የቴክኖሎጂ ዘርፉን መምራት ያለበት የግሉ ዘርፍ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

እንደ መንግስት የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ያሉ ሕጎችን እያሻሻልን ነው ያሉት ሚኒስትሩ÷ የግሉ ዘርፉ ደጋፊ ከመሆን ወጥቶ ሃብትና የስራ እድል ፈጣሪ እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

ሚኒስቴር መስሪያቤቱ እና የአሊባባ የሥራ ፈጠራ ፕሮግራም በጋራ ባዘጋጁት ሥልጠና ልምድ ማግኘታቸውንና ይህንን ልምድ በመጠቀም መድረኩን ወደ ከፍተኛ አቅም እንደሚቀይሩት መናገራቸውን ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!