የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ነብያት ለአፍሪፖል በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ገለጻ ሰጡ

By Meseret Demissu

February 04, 2021

አዲስ አበባ ፣ ጥር 27 ፣ 2013 (ኤፍ ቢ ሲ) በአልጄሪያ የኢፌዴሪ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ነብያት ጌታቸው ተቀማጭነቱን በአልጀርስ ላደረገው የአፍሪካ ህብረት የፖሊስ ተቋማት ትብብር ማዕቀፍ (አፍሪፖል) ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጣሪቅ ሸሪፍ በወቅታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ገለጻ ሰጥተዋል።

ገለጻውም በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል የተካሄደውን የህግ ማስከበር ሥራና የሰብዓዊ ዕርዳታ እንቅስቃሴ፣ በኢትዮጵያና ሱዳን ድንበር ግጭትና የህዳሴ ግድብ ድርድርን የተመለከተ ነው።

አምባሳደር ነብያት ከዶክተር ጣሪቅ ሸሪፍ ጋር ባደረጉት ውይይት÷ የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ያደረገው የህግ ማስከበር ዘመቻ መጠናቀቁንና በክልሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ በመንግስትና በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ትብብር ለማድረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አውስተዋል፡፡

አያይዘውም ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት  የስደተኞች ኮሚሽነር በስፍራው ተገኝተው ጉብኝት ማድረጋቸውንና በቀጣይ ሥራዎች ዙሪያም ከመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ውይይት መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተከሰተው የድንበር ግጭትም ታሪካዊ ዳራውን በመግለጽ ኢትዮጵያ ሱዳን ወደ ቀድሞ ሥፍራዋ ተመልሳ ድርድሩ መካሄድ እንዳለበትና ችግሩ ሊፈታ የሚችለውም በውይይት ብቻ መሆኑን እንደምታምን ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ሸሪፍ በበኩላቸው÷ በአፍሪካ ውስጥ ግጭቶች እንዳይበራከቱ ተቋማቸው በህግ ማስከበር ዙሪያ ከአባል ሃገራት ጋር የትብብርና የአቅም ግንባታ ሥራዎች እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

አያይዘውም ድንበር ዘለል ግጭቶች እንዳይባባሱ በውይይት መፍታት አስፈላጊ ነው ማለታቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

አፍሪፖል በአፍሪካ ኀብረት በአባል ሃገራት የፖሊስ ተቋማት መካከል ሁለንተናዊ ትብብር ለማድረግ የተቋቋመ አካል ሲሆን ተቀማጭነቱም አልጄሪያ አልጀርስ ከተማ ነው፡፡

Aaከፌስቡክ ገፃችን በተጨማሪ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

የፋና ድረ ገጽ https://www.fanabc.com/ ይጎብኙ፤

ተንቀሳቃሽ ምስሎችን ለማግኘት የፋና ቴሌቪዥን የዩቲዩብ ቻናል https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ሰብስክራይብ ያድርጉ

ፈጣን መረጃዎችን ለማግኘት ትክክለኛውን የፋና ቴሌግራም ቻናል https://t.me/fanatelevision ይቀላቀሉ

ከዚህ በተጨማሪም በትዊተር ገጻችን https://twitter.com/fanatelevision ይወዳጁን

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!